ቀጥታ፡

የነዳጅ አቅርቦት ችግርን ለመቆጣጠር መንግሥት ያሳለፋቸውን ወሳኔዎች በአግባቡ እየተገበርን ነው- የነዳጅ ማደያዎች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018(ኢዜአ) ፦ በመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የተፈጠረውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመቆጣጠር መንግሥት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በአግባቡ እየተገበሩ እንደሚገኝ የመዲናዋ አገልግሎት ሰጪ የነዳጅ ማደያዎች ገለጹ። 

የመካከለኛው ምስራቅ ግጭትን ተከትሎ በርካታ ዓለም ሀገራት በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለለት ላይ የተፈጠረውን አስቸጋሪ መስተጓጎል መቋቋም የሚያስችል ጥብቅ የቁጠባ መመሪያዎችን በማሳለፍ ላይ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ሁኔታን ተከትሎ በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቋቋም ዜጎች ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀሙ ማሳሰባቸው ይታወቃል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትን በቁጠባና በጥብቅ ቁጥጥር መምራት የሚያስችል የተፅዕኖ መቋቋሚያ እቀባዎችን አሳልፏል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የመንግሥትን የነዳጅ ቁጠባና ቁጥጥር ዝርዝር  ውሳኔዎችን ይፋ አድርገዋል።

በዚህም ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣ ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች በቀጥታ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ፣ የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች፣ ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮችና የከተማና ሀገር አቀፍ የብዙሃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በማደያዎች ቅድሚያ እንዲያገኙ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራርን አብራርተዋል።

ህብረተሰቡም ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀም፣ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን የመጠቀም ስልትን መከተል፣ የእግር ጉዞ ባህልን ማጎልበት፣ አላስፈላጊ የጉዞ ፕሮግራሞችን መሰረዝና ማቆም፣ የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም እና በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ የነዳጅ አገልግሎት የሚሰጡ ማደያዎች ለኢዜአ እንዳሉትም፤ የነዳጅ አቅርቦት ሰለንሰለቱን በቁጠባና በጥብቅ ቁጥጥር ለመምራት መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ አክብረው እየሰሩ ይገኛል።

የቀበና ኦላ ነዳጅ ማደያ ኃላፊ አማረ ሽታሁን፤ የመንግሥትን የነዳጅ ቁጠባና ቁጥጥር የውሳኔ አቅጣጫ በማክበር አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የቄራ ኖክ ማደያ የኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ ወልደማርያም ፉጃው፤ በነዳጅ አቅርቦት የተፈጠረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ምርትን በቁጠባና በመንግሥት ውሳኔ መሰረት እያቀረብን ነው ብለዋል።

የካምፖ አስመራ ነዳጅ ማደያ ተቆጣጣሪ ጥበቡ በቀለ፤ በመንግሥት የውሳኔ ሃሳብ መመሪያ መነሻነት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ተሽከርካሪዎች በዲጂታል ሥርዓት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቀጣይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ የመንግስትን መመሪያ በማክበር ለነዳጅ ቁጠባ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የተሽከርካሪ ባለንብረቶችና ዜጎች ዓለም አቀፉ ተፅዕኖ እስኪቀረፍ ድረስ ነዳጅን በቁጠባ በመጠቀም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የሚችልን ጫና ለመቋቋም ገንቢ ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም