የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ በ25ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ይመለሳል።
ፕሪሚየር ሊጉ ላለፉት 18 ቀናት ተቋርጦ ነበር።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከባህር ዳር ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኝ ጊዜ ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በ10 ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ37 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በውድድር ዓመቱ 24 ጨዋታዎችን አከናውኖ በስድስቱ ድል ሲቀናው አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ 13 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 17 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ባህር ዳር ከተማ በ31 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። ደረጃውንም ወደ ሶስተኛ ከፍ ያደርጋል።
ባህር ዳር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
በሌላኛው መርሐ- ግብር መቻል ከምድረ ገነት ሽሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቻል እስከ አሁን በሊጉ 24 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ዘጠኝ ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። በዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በ24ቱ ጨዋታዎች ላይ 29 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 19 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ36 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ምድረ ገነት ሽሬ በበኩሉ ካከናወናቸው 24 ጨዋታዎች መካከል ስድስት ጊዜ ድል ሲቀናው በዘጠኙ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 16 ግቦችን ሲያስቆጥር 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ምድረ ገነት ሽሬ በ27 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው መቻል ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
ምድረ ገነት ሽሬ ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ድሬዳዋ ከተማ ከፋሲል ከነማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ድሬዳዋ ከተማ በ28 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። ፋሲል ከነማ በ35 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች የተሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ፋሲል ከነማ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ከድል የራቀ ሲሆን ማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ያስችለዋል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ሸገር ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ30 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። አርባምንጭ ከተማ በ19 ነጥብ የመጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሸገር ከተማ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። አርባምንጭ ከተማ ድል ከቀናው በሊጉ አራተኛ ድሉን ያገኛል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት እስከ መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና በ45 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 10 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ነው።
የፋሲል ከነማው ታምራት እያሱ በስምንት ግቦች ይከተላል።