ምክር ቤቱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅን አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ስርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅን አፀደቀ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018 (ኢዜአ)፦ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና በፍትህ ዘርፍ ለሚደረገው ሪፎርም ትልቅ እርምጃ ነው ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅን ቁጥር 1410/2018ን በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አዋጁ ጊዜ ተወስዶብት በአግባቡ ውይይት እና ምክክር ተደርጎበት የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
አዋጁ ዘመኑ ከደረሰበት የወንጀል ሳይንስ ጋር የተጣጣሙ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገሪቷን የጠንካራ ፍትህ ተቋም ባለቤት በማድረግ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አበርክቶት የሚኖረው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ የኮሚቴውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
አዋጁ የሀገሪቱን የፍትህ ሥርዓት ለማዘመንና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ታቅዶ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የሀገርን፣ የሕዝብንና የግለሰቦችን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ ረገድ መንግስት ያለበትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ መርሆዎችና እሴቶች በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው አዋጁ ቀደም ሲል በነበረው ሕግ ያሉ ክፍተቶችን የሚያስወግድ ነው ብለዋል።
በተለይም የሚስተዋሉ የክስ መጓተቶችና የፍትህ መዘግየቶችን በሕግ እንደሚቀረፉ አባላቱ ገልጸዋል።