ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን የትርክት ስብራት የሚጠግን መሰረት ጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን የትርክት ስብራት የሚጠግን መሰረት ጥሏል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 24/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን የትርክት ስብራት የሚጠግን መሰረት መጣሉን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ምሁራንና የሃሳብ መሪዎች የሀገርን ዕድገትና የዜጎችን አንድነት የሚያስጠብቅ ብሔራዊ ዕሳቤን በማስተጋባት ለአዎንታዊ ትርክት ግንባታ ገንቢ ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ የጋራ ዕድገትን በማሳለጥ የኢትዮጵያን የትርክት ስብራት የሚጠግን መሰረት ጥሏል።
አዎንታዊ ትርክት የተረጋጋ ሀገረ መንግስት በማነፅ የበለፀገ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ለአብነትም አሜሪካና ሲንጋፖር ያለፉበት አዎንታዊና አሰባሳቢ የትርክት ግንባታ ሂደት ልዕለ ኃያልነትንና የኢኮኖሚ ብልፅግናን ማረጋገጥ ያስቻለ ስኬት እንዳጎናጸፋቸው አስገንዝበዋል።
በአንፃሩ በአሉታዊ መንገድ የተገነባ ትርክት የዜጎችን ትስስር በማላላት ለዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ሳንካ በመፍጠር ሀገርን እስከመበተን የሚያደርስ አደጋ እንደሚያስከትል አስረድተዋል።
በዚህም አዎንታዊ ትርክት ግንባታ በማጠናከር የሀገርን ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያረጋግጥ የወል እውነትን መገንባት ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በፊት የዜጎችን ነባራዊ ሃቅ በመካድ በተቃርኖ ጎራ የቆሙ ፍፁም ነጣጣይና ጨፍላቂ ትርክቶች ሲስተጋቡ እንደነበር አስታውሰዋል።
ለአብነትም ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ እስከ 1966ቱ አብዮት ድረስ የነበረው ትርክት ብዝኅነትን እንደስጋት የሚወስድና የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ማንነትና ገፅታ የካደ ጨፍላቂና አግላይ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከ1966ቱ አብዮት በኋላም ከፋፋይ፣ ነጣጣይ፣ በማህበረሰብ ማንነት ላይ የሚያተኩርና ሀገራዊ አንድነትን የሚያገል እንደነበር ጠቁመው፤ ይህም ኢትዮጵያን ፅንፍ በረገጡ እሳቤዎች ውድ ዋጋ እንድትከፍል ማስገደዱን አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ፅንፍ የረገጡ ትርክቶችም በብሔራዊ ጀግኖችና የጋራ ምልክቶች ሳይቀር የጋራ ዕይታና አቋም እንዳይኖር በማድረግ በጦርነትና ግጭት ውስጥ እንድንቆይ አድርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በደምና አጥንታቸው ለጭቁን ህዝቦች ሁሉ ትዕምርት የሚሆነውን የዓድዋ ድል መጎናፀፍ የቻሉ ስልጡን ህዝቦች ሆነው ሳለ በስሁት ትርክት ምክንያት ውድ ዋጋ ሲከፍሉ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ላይ ቃል ከገቡባቸው ዋና ዋና ሃገራዊ እሳቤዎች መካከል የወል ትርክት ግንባታ ወሳኙ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በዚህም በሀገራዊ ለውጡ ማግስት አሰባሳቢና የወል እውነት በመገንባት ቁርሾና አለመግባባቶችን በሰለጠነ የንግግር፣ ዕርቅና ምክክር መፍታት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል።
የሚዲና ኮሙዩኒኬሽን፣ የህዝብ ውይይቶች፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና የልማት አቅጣጫዎች የሚያሰባስቡና ከትናንት የተሻገሩ ዕዳዎችን ወደ ምንዳ የሚቀይሩ ሥራዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያን በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ያሸበረቀና ዘመናትን የተሻገረ የጋራ ታሪክና ዓድዋን መሰል ዓለምአቀፍ የጋራ እሴት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አንስተዋል።
አፍሪካዊያን ከባርነት ቀንበር ነፃ የወጡበትን የሚዘክሩበት ሃውልት አላቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ቀንዲል የሆነችው ኢትዮጵያ የዓድዋ ድልን የሚዘክር ጡብ እንዳልነበራት አንስተዋል።
ለዚህም ሀገራዊ ለውጡም የኢትዮጵያዊያን የጋራ ገድልና ታሪካዊ ክዋኔ የሆነውን የዓድዋ ድል የሚዘክርና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ መሳሪያ የሆነ ዘካሪ ሃውልት ማቆሙን ጠቅሰዋል።
የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዳግማዊ ዓድዋ የሆነው ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የልብ ትርታ ያለበት ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ወሳኝ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።
የበለፀገች ኢትዮጵያ የዜጎቿ የኩራት ምንጭ ትሆናለች ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ኢትዮጵያዊያን አዎንታዊ ትርክት ግንባታን በማጎልበት ለሀገር ዕድገት መተባበር አለባቸው ብለዋል።
በዚህም ቀጣይ የኢትዮጵያ ምሁራንና የሃሳብ መሪዎች የሀገርን ዕድገትና የዜጎችን አንድነት የሚያስጠብቁ ብሔራዊ እሳቤዎችን በማስተጋባት ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ገንቢ ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።