የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ለሀገራዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የተሟላ ቁመና ላይ ናቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ለሀገራዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የተሟላ ቁመና ላይ ናቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018 (ኢዜአ)፦ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ለሀገራዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የተሟላ ቁመና ላይ ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የተሟላ ዝግጅትና በማድረግ የተቀናጀ አሰራር መዘርጋቱም ተመላክቷል።
2ኛው ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፍረንስ "የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ቅንጅት ለሀገራዊ ሰላም እና ደኅንነት!" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።
በየአምስት ዓመቱ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ የፀጥታና የደኅንነት አመራሮች ተገኝተዋል።
በዚሁ ኮንፈረንስ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የጸጥታና ደኅንነት ሁኔታዎች የተገመገሙ ሲሆን የኢትዮጵያ የፀጥታና ደኅንነት ምኅዳርና ዝግጁነትም በጥልቀት ውይይት ተደርጎበታል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለችበትን የጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታና የጸጥታ ተቋማት የሪፎርም ስኬቶች በዝርዝር አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በድል እና በዕንቅፋት መካከል እየተጓዘች መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሕዝቧ ታታሪነትና እያደገ ያለው ኢኮኖሚ እንደ ትልቅ ዕድል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በኢትዮጵያ የኃይልና የሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ የሚቀነባበሩ ሤራዎችን በጽናት በመቀልበስና በመመከት፣ ለአህጉሩ ፋና ወጊ የሆነ የለውጥና የሀገር ግንባታ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል በመዘመናቸው፣ ሀገራዊና ቀጣናዊ ሥጋቶችን በብቃት የመቀልበስ አቅም ፈጥረዋል ነው ያሉት።
ተቋማቱ ችግሮችን ወደ ዕድል በመለወጥና መሥዋዕትነት በመክፈል ለሀገራዊ ለውጡ ስኬት የላቀ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የቀረበውን የሰላም አማራጭ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚመለሱ ወገኖች ቁጥር መጨመሩ ለሀገር ሰላም መረጋገጥ ትልቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት የወሰዳቸው ፖለቲካዊ ርምጃዎችና የፀጥታ ተቋማቱ ቅንጅታዊ ሥምሪት ሀገሪቱን ከግጭት አዙሪት በማውጣት ረገድ ውጤታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት ያለውና ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የዘመኑ ትውልድ ይህንን ብሔራዊ ጥቅም ሳያሳካ ወደ ኋላ እንደማይመለስ አስታውቀዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ባለብዙ ፍላጎቶችና ስትራቴጂካዊ ስምሪቶች የሚታዩበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህንን ፈተና በብቃት ለመሻገርና የሚገኙ አጋጣሚዎችን ለተሻለ ዕድል ለመጠቀም የዜጎች ትብብር ወሳኝ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህም መሰረት በሲቪል፣ በፀጥታና በመከላከያ ተቋማት መካከል ያለው ትብብር ይበልጥ ሊጎለብት እንደሚገባና ተቋሙም ይህንኑ ቅንጅት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የኢትዮጵያን ሰላም፣ ፀጥታና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ተቋማዊ ቁመናውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ሰፊ የለውጥ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎች ለማሳካትም ከሁሉም የፌደራልና የክልል የፀጥታ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራርና የጋራ ስምሪት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህና አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የተሟላ ዝግጅትና በማድረግ የተቀናጀ አሰራር መዘርጋታቸውን አረጋግጠዋል።
ምርጫው ዴሞክራሲን ለማጽናትና ሀገረ መንግሥቱን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።