ቀጥታ፡

የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስር መጠናከር ተወዳዳሪና ብቁ የሰው ኃይልን ለማፍራት አግዟል

ወልቂጤ፤መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦የዩኒቨርሲቲ እና ኢንዱስትሪ ትስስር መጠናከር ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ተወዳዳሪና ብቁ የሰው ኃይልን ለማፍራት እያገዘ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ትስስር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሃብቴ ዱላ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲዎች ትስስሩ የኢንዱስትሪው ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ተወዳዳሪና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት አግዟል፡፡

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰለጠነ የሰው ኃይልን ከማፍራት በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማውጣት ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑና አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች እንዲስፋፉ ድርሻቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የተቋማት ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዴስክ የተቋማት ትስስር ባለሙያ አቶ ተካልኝ ባህሩ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰሩ ሀብትና እውቀትን በማቀናጀት ውጤት እንዲገኝ አድርጓል ብለዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት የጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲጎለብቱ እገዛ ማድረጉንም አክለዋል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደምሰው ባቾሬ በበኩላቸው፥ የዩኒቨርስቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር መጠናከር ምርታማነትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ፣የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ማገዙን ጠቁመዋል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የተካሄደው የምክክር መድረክም በዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት በጋራ ለመፍታት ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በምከክር መድረኩ ላይ የተሳተፉት የደስታ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ወልዴ የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስሩ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ ምርታማነት በማደጉም ለአንድ ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸው፥ በቀጣይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል።

የእንጨት ውጤቶችን በጥራት ለማምረት የሚያስችላቸውን የሰው ኃይል ለማግኘት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ያለው ትስስር እንዳገዛቸው የሚናገሩት ደግሞ የብሉ ኤሌፋንት ድርጅት ሽያጭና ግዥ ባለሙያ አቶ ፍቅር ታደሰ ናቸው።

ተቋሙ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በፈጠረው ትስስር ለበርካታ ተማሪዎች የተግባር ትምህርት ዕድልን እንዲያገኙ በማድረግ የእውቀት ሽግግር ላይ መስራቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም