ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብን ችግሮች ለመፍታት ከፌዴራል መንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆነን መስራት ይገባናል - ኬርያ ኢብራሂም

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018 (ኢዜአ) ፡- የትግራይን ህዝብ ችግሮች ለመፍታት ከፌዴራል መንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆነን መስራት ይገባናል ሲሉ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም ተናገሩ።

ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም ቀደም ሲል የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ በመሆን ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉትም በለውጡ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን መሪዎች ከመንግስት ጋር ያሏቸው ልዩነቶች ዋነኛ መነሻቸው በአገሪቱ “እኔ የማልቆጣጠረውና ለእኔ የማይታዘዝ አመራር መኖር የለበትም” የሚል ያልተገደበ የስልጣን ጥማት ነው።

በወቅቱ የተለወጠ ስርዓት በሌለበት የለውጡ መንግስት ሕገ-መንግስትና ፌዴራላዊ ስርዓቱን ሊያፈርስ የመጣ አሃዳዊ ስርዓት ነው በሚል ፍረጃ ህዝብን በማሳሳት ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲገባ አድርገነዋል ብለዋል።

አሁንም የለውጡ መንግስት ሪፎርም ከማድረግ ባሻገር የቀየረው ሕገ-መንግስትና ፌዴራላዊ ስርዓት በሌለበት ሁኔታ የትግራይ ህዝብን በተመሳሳይ ፕሮፓጋንዳ እንደገና ለማታለል መሞከር ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸው ህዝብም እውነታውን ሊረዳ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አሁን በትግራይ የሚስተዋለው ቀውስ ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የፕሪቶሪያን ስምምነት በመጣስ ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል ሻዓብያ ጋር የፈጠረው ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በተሳሳተ ስሌት ህዝብን በለውጡ መንግስት ላይ በማነሳሳት ከባድ ዋጋ እንዲከፍል አድርገነዋል ያሉት ወይዘሮ ኬርያ፤ አሁንም ካለፈው ስህተት የማይማር የህወሓት ቡድን ወደ ሌላ አውዳሚ ጦርነት ለመግባት ሻዓብያ ከተባለው የኢትዮጵያ ጠላት ጋር በመሆን የጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የሻዓብያ አገዛዝ ፍላጎት የተዳከመች እና የተበታተነች ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ኬርያ፤ ምርጫና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ከማያውቅ ፍጹም አምባገነናዊ መንግስት ጋር በመሰለፍ የሚፈታ የህዝብ ችግር እንደሌለም ተናግረዋል።

በመሆኑም የትግራይ ወጣቶች ወንጀለኛው የህወሓት ቡድን ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር በመሆን የሚያደርገውን የጦርነት ዝግጅት ለማስቀረት እና አላስፈላጊ መስዋዕትነት ላለመክፈል ከፌዴራል መንግስት ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ መስራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም