ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን ለማበረታታት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጦች ተገኝተዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ በለውጡ ዓመታት የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅን በማሻሻል ህጋዊ አሠራርን ለማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጦች መገኘታቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በበኩሉ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ገልጿል። 

ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓም ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ መንግሥት የዜጎችን ደህንነትና መብት ማስከበርን ቀዳሚ የዲፕሎማሲ አጀንዳ አድርጓል።

ይህን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራትም በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ዜጎች መብታቸው እንዲከበር ከሀገራቱ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በማድረግ ዜጎች በሕግ የተጠበቀ ክብር እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡ 

በዚህም የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅን በማሻሻል፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ለዜጎች ጥበቃ ቅድሚያ እንዲሰጡ ማድረግ ለአብነት ይጠቀሳሉ። 

ዜጎች ከሀገር ከመውጣታቸው በፊት አስፈላጊውን የክህሎትና የዝግጅት ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉም ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል። 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ህገ-ወጥ ስደትን ለመቀነስ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል። 


 

በተለይም በብዛት ኢ-መደበኛ ፍልሰት የሚዘወተርባቸውን አካባቢዎች በመለየት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።  

በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው ችግሮች ያጋጠሟቸውን የስደት ተመላሾችንና ማህበረሰብ ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸውንም ነው የተናገሩት።

የህጋዊ ስራ ስምሪት እድሎች መስፋፋት፣ ከስደት የተመለሱ ዜጎች በሀገራቸው የስራ ፈጠራ ላይ እንዲሰማሩ የተደረጉ ድጋፎች በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ ለመሆን መቻላቸውንም  አንስተዋል።

በመሆኑም  ህገ ወጥ ስደትን ከመቀነስ አኳያ ለውጦች መገኘታቸውን ገልጸዋል። 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ይገልጻሉ። 


 

ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች ቁጥር 300 ሺህ የሚደርስ እንደነበረ አንስተዋል። 

በ2018 በጀት ዓመት ሰባት ወራት ወደ 450 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ደህንነታቸውና መብታቸው ተጠብቆ በተለያዩ ሀገራት መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

ይህም የዜጎችን ክብርና ደህንነት ከመጠበቅ አኳያ ከፍ ያለ ትርጉም አለው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም