ስምንት ዓመታት፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ወደ ዘመናዊ እና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ - ኢዜአ አማርኛ
ስምንት ዓመታት፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ወደ ዘመናዊ እና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ
ባለፉት ስምንት ዓመታት፣ ኢትዮጵያ ከአግላይ፣ ከልካይ ከሆነው ወደ አስቻይ የኢኮኖሚ ምኅዳር፣ የኢኮኖሚ ሞዴል ተሸጋግራለች፡፡
በዚህም ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን የሚቋቋም፣ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ አቅጣጫን ወደሚከተል፣ ትክክለኛ ውድድር ላይ ወደ ተመሰረተ፤ በገበያ የሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጥልቅ የለውጥ ጉዞ አድርጋለች።
ከ2010 ዓ.ም በፊት የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት በቂ የሥራ ዕድል አልፈጠረም፤ የወጪ ንግድ አማራጮች ጠባብ ነበሩ፤ በውጭ ብድር ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ነበር። በእነዚህ እና ሌሎች አሳሪ ምክንያቶች የተነሣ በመዋቅራዊ ድክመቶች ተተብትቦ ቆይቷል።
ከለውጡ በፊት የግብርና ምርታማነት መጠነኛ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የግብርና አቅም በአግባቡ ያልተለየበት ሲሆን ተግባር ተኮርም አልነበረም፡፡
በዚህም ዋነኛ ኢኮኖሚያችን የሞፈርና የዝናብ እሥረኛ ከመሆን ትርጉም ባለው መልኩ ማውጣት አልቻለም፤ ውጤቱም ከሁሉም የአምራች ዘርፎች ከወጪ ንግድ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ሳይሻገር ለረጅም ዓመታት ቆይቷል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ከሀገር በቀል ኢኮኖሚው ጋር ያላቸው ትሥሥር ደካማ በመሆኑ እንደ ገለልተኛ ደሴቶች ይታዩ ነበር። ለውጡ በፊት የነበረው የኢኮኖሚ ስርዓት የማክሮ ኢኮኖሚ ተጋላጭነትን ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል።
በውጭ ብድር የተከናወኑ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች በቂ የውጭ ምንዛሬ “ማመንጨት ባለመቻላቸው፤ የዕዳ ጫናው እንዲባባስ አድርገዋል። ለግል ዘርፍ እና ለዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ልማት በነበረው የተንሸዋረረ አካሄድ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ ፋይናንስ እና ማዕድን ዘርፎች ያልዳበሩ ወይም ለግል ዘርፉ ዝግ የሆኑ ነበሩ፡፡ እነዚህ አዝጋሚ አካሄዶች የፈጠራ ሥራዎችን፣ የግል ኢንቨስትመንትን እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን እና የመዋቅራዊ ሽግግርን ገድበውት ቆይተዋል።
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት፣ አዳዲስ የዕድገት ምንጮችን ለመክፈት እና የማከሮ ኢኮኖሚ መዛባት ችግሮችን ለማረም የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ የለወጥ አጀንዳን ተግባራዊ አድርጋለች። የነበረውን የማከሮ ኢኮኖሚ ችግርን በመጋፈጥ፣ ሀገራዊ ዐቅምን በማሰባሰብ፣ ብርሃን ፈንጣቂ ውጤቶች አስመዝግባለች፡፡
የግብርና አብዮት እና የምግብ ሉዓላዊነት
የለውጡ ዋነኛ ምሰሶ ግብርናን ወደ ምርታማነት፣ ወደ ብዝኃነት እና ወደ ዘላቂ አስተማማኝ ዐቅም ማሸጋገር ነው። ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ስኬትን ተቀዳጅታለች፡፡ ኢትዮጵያ በስንዴ እርሻ ባስመዘገበችው አመርታ ሙሉ በሙሉ እራሷን መቻል ችላለች።
በዚህም በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ የስንዴ አምራች ለመሆን በቅታለች። የሰብል ብዝኃነትም በከፍተኛ ፍጥነት ጨምሯል፤ በብዝሃ ሰብል ልማት አማራጭ አማካኝነት በተለይ የሩዝ፣ የቅባት እና ሌሎች ለኢንደስትሪ ልማት የሚውሉ ሰብሎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምሩ ማድረግ ተችሏል። የእንስሳት ሀብት እና ከፍተኛ ዕሴት ያላቸው የግብርና ምርቶች ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ይገኛል። ዓመታዊ የዕንቁላል ምርት 9.4 ቢሊዮን ደርሷል፤ የወተት ምርት 13 ቢሊዮን ሊትር የሚገመት የደረሰ ሲሆን፣ የሥጋ ምርትም ወደ አሥር እጥፍ በሚጠጋ መጠን አድጓል። እነዚህ ውጤቶች ጤናማ እና ሚዛኑን የጠበቀ የአመጋገብ ስርዓት፣ ስርዓተ ምግብ መሻሻል እና ብዝኃነቱ ወደ ተጠበቀ የገጠር ገቢ ምንጮች የተደረገውን ሰፊ ሽግግር ያሳያሉ።
9.5 ሚልዮን አርሶ አደሮችን በ12.8 ሚልዮን ሄክታር መሬት ላይ ያሳተፈው የኩታ ገጠም እርሻ በመዋቅራዊ ለውጥ ላይ የሚለካ ውጤቶችን አስገኝቷል፡፡ ይሄም የ29 በመቶ የምርታማነት ዕድገት እና የ18 በመቶ የገቢ ጭማሪን ያካትታል። በአጠቃላይ የግብርና ምርት በሰባት ዓመታት ውስጥ ከ41.7 ሚልዮን ቶን ወደ 150 ሚልዮን ቶን ከፍ ብሏል፡፡
ይሄም የግብርና ዘርፍ ለተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት የተሻለ አስተዋፅዖ እንዲኖረው አስችሏል። እንዲሁም ለተመዘገበው ከፍተኛ የስራ ዕድል በከተማም ይሁን በገጠር ዓመታዊ አበርክቶ አድርጓል። የግብርና ልማት እመርታ ለኤክስፖርት ገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረገ ሲሆን የቡና ምርት በእጥፍ አድጎ ወደ አንድ ሚልዮን ቶን የተጠጋ ውጤት ተመዝግቦ፤ በ2017 ዓ.ም ብቻ 2.65 ቢልዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ዕድገት
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ከ48 ቢልዮን በላይ ችግኞች ተተከለዋል፡፡
12.5 ሚልዮን ሄክታር መሬት ደግሞ እንዲያገግም ተደርጓል። የሀገሪቱ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 በመቶ በ2017 ዓ.ም ወደ 23 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ይህ ቁልፍ እርምጃ የአፈር መሸርሸርን ከመቀነሱም በላይ ለኢኮኖሚው ድጋፍ ሆኗል። ይህም ለግብርና እና ለስርዓተ ምግብ ለውጥ አስተዋፅዖ እያደረገ ሲሆን ለቡና ምርት አቅርቦት መሻሻል፣ የኤከስፖርት የውጭ ምንዛሬ ግኝት መሻሻል ከፍ ያለ አስተዋፅዖ አድርጓል። በአጠቃላይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ ጥበቃ፣ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ያለውን ቁርኝት በተግባር ያሳየ ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እና የወጪ ንግድ አቅጣጫ
የኢንዱስትሪ ንድፉ አምራች ኢንዱስትሪውን፣ ሎጂስቲክሱን እና አገልግሎቶችን ወደ ሚያቀናጁ "ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች" (Special Economic Zones) የሚያስገኙትን ጠቀሜታ ለማረጋገጥ ትኩረት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እና ሌሎች አምራች ዘርፎች ጋር የኢኮኖሚ ትሥሥር እንዲጠናከር ተደርጓል።
በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚገኙ ባለ ሀብቶች ቁጥር በ2010 ዓ.ም 36 ኩባንያዎች ነበሩ፤ አሁን ላይ ከ200 በላይ ባለ ሀብቶች በልዩ ቀጣናው እየተሳተፉ ናቸው:: የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ድርሻም 65 በመቶ የሚጠጋ ሆኗል። ይህ ሽግግር ኢንዱስትሪን ከተገነጠለ ደሴትነት ወደ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ሥነ ምኅዳር መለወጡን ያሳያል፡፡ በዚህም ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ለወጪ ንግድ የሚቀርበው ምርት በየጊዜው እያደገ ሲሆን በቀጣይም በተኪ ምርቶች ላይ ጥገኛ የሆነውን ከአምራች ዘርፎች የወጪ ንግድ አማራጭ እያሰፋ ይገኛል።
ማዕድን፣ የገቢ ንግድን መተካት እና የወጪ ንግድ ማሳደግ
ባለፉት ስምንት ዓመታት፤ የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት የማዕድን ሀብቷ ነው:: የማዕድን ዘርፍ ከለውጡ በፊት የልማት አሳላጭ ሳይሆን ርግማን ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ ይሄንን ዕይታ በመቀየር ዘላቂ ለሆነ ልማት እና የህብረተሰብ ተጠቃሚነት ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ እንዲያገለግል ዘርፉ በአዲስ መልክ እንዲቃኝ ተደርጓል። በዚህም የማዕድን ዘርፍ ሚና እና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽዖ ማሳደግ ተችሏል። የወርቅ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እድጎ ወደ 39 ቶን ተጠግቷል፡፡
ከወርቅ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢም በ2017 ዓ.ም በግምት 3.5 ቢልዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አስገኝቷል፡፡ ይሄም ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ከ45 በመቶ በላይ ድርሻ ይዟል። ገቢ ንግድን በሀገር ውስጥ የመተካት ጥረቶችም ውጤት አምጥተዋል፡፡ ይሄም የድንጋይ ከሰል ገቢ ንግድን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ተተክቷል፡፡ የሲሚንቶ ምርት ዓመታዊ የማምረት ዐቅምን ከ20 ሚልዮን ቶን በላይ በማድረስ ራስን የመቻል ጉዞው ውጤት እያስገኘ ነው።
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የፋይናንስ ተደራሽነት
የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ለግል ዘርፉ ከፍት መሆኑ በአህጉሩ ፈጣን ከሚባሉ የዲጂታል ዕድግቶች አንዱን አስመዝግቧል። የሞባይል ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ37.9 ሚልዮን ወደ 87.9 ሚልዮን በማደግ ተደራሽነትን እና አካታችነትን አስፍቷል። የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶች ከ58 ሚልዮን በላይ ተጠቃሚዎችን አፍርቷል፡፡ የገንዘብ ዝውውሩም ከ7.5 ትሪልዮን ብር በላይ በመሻገር የፋይናንስ ተደራሽነት እና አካታችነት እውን ሆኗል። የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እያረጋገጡ ይገኛል፡፡
ከዚህ የተነሳም የባንኮች ብድር ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሁኔታ ለመንግሥት እና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበረውን፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተናበበ ሁኔታ የግል ዘርፉ ድርሻ ከፍተኛ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም የግል ዘርፉ ከአጠቃላይ በባንኮች የሚሰጠው ብድር የሚያገኘው ድርሻ ከ85 በመቶ በላይ ሆኗል። የመንግሥት ባንኮችን መልሶ ማዋቀር እና የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት በማስጠበቅ የገንዘብ ፍሰትን አሻሽሏል፤ የሀብት ጥራትን ጨምሯል፤ የፋይናንስ ዘላቂነትን አጎልብቷል።
የበጀት አጠቃቀም (ዲስፕሊን) እና መዋቅራዊ ለውጥ
የቅርብ ጊዜ ስኬቶች መለያ ባህሪ ለበጀት አያያዝ እና አጠቃቀም የተሰጠው ቁርጠኝነት ነው። ከ2010 ዓ.ም በፊት ከነበረው በተቃራኒ፤ ማሻሻያዎች የተተገበሩት በውጭ የንግድ ብድር ምክንያት የመጣውን የመንግሥት ፋይናንስ ጫና በመሰረታዊነት ለመቀየር የነበረውን ጥገኝነት በማስወገድ ነው። በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች፣ የተሻሻለ የፕሮጀከቶች አመራረጥ እና ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸውን ዘርፎች የማስተካከል ሥራዎች ብክነትን ቀንሰዋል፤ የመንግሥትን ፋይናንስም አጠናክረዋል።
የከተሞች አብዮት እና የሰው ሀብት ልማት
ከተሞች የዕድገት ሞተር መሆናቸውን ኢትዮጵያ ትገነዘባለች፡፡ ኑሯችንን እና እኗኗራችንን ለማዘመን፣ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እና መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋጋጥ ከተማ ትልቁ መሠረት ነው። ከተማ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጫችንን በማስፋት ዘርፈ ብዙ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ይፈጥራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢኖቬሽን እና አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመሳብ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ቁልፍ መሠረት ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ በከተሞች ልማት፣ በመሠረተ ልማት እና በቤት ልማት ላይ የግል ዘርፉን ባሳተፈ መልኩ ኢንቨስት አድርጋለች። በተቀናጀ የኮሪደር ልማት፤ ከተሞችን ለመኖሪያ፣ ለቱሪዝም፣ ለፈጠራና ለቢዝነስ ምቹ ማድረግ ተችሏል ።
ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የቢዝነስ ማዕከል እንዲሆኑ የተቀናጀ የከተማ ልማት ባለፉት ዓመታት ተከናውኗል።
የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሮ ወደ 56 ከተሞች ሰፍቷል። በዚህም ከተሞች ለኑሮና ለሥራ ምቹ ከመሆን በተጨማሪ የከተሞችን ቀጣይ የዕድገት አቅጣጫ የቀረጸ ሆኗል።
አዲስ የኢኮኖሚ ቅኝት
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ በመንግሥት ኢንቨስትመንት ጥገኛ ከሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና አቅጣጫ ወጥታለች። በዚህም በዘርፎች ትስስር እና መሰናሰል፤ በምርታማነት ላይ የተኮረ፤ በግል ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ እና በመዋቅራዊ ሽግግር ላይ ወደ ተመሰረተ ሞዴል እየተሸጋገረች ነው።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በፋይናንስ፣ በዲጂታላይዜሽን እና በከተማ ልማት የታዩት ማሻሻያዎች ለኢኮኖሚ አስተዳደር ያለውን ተግባራዊ እና ውጤት ተኮር አካሄድ የሚያንፀባርቁ ናቸው። ምንም እንኳን ተግዳሮቶች ቢኖሩም፤ አሁን ያለው የኢኮኖሚ ሽግግር ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ዕድገት መሠረት እየጣለ ይገኛል። ይህም ተወዳዳሪ እና ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት መዋቅራዊ ማሻሻያ፣ ውጤታማ የበጀት አጠቃቀም እና የፖሊሲ ሁኔታዎችን የመቀየርን አስፈላጊነት ያሳያል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ ራሷን ወደ መቻል እና ወደ ተሻለ መጻኢ ጊዜ እና ኢትዮጵያ ወደ ተነሳችበት በሚወሰድ መንገድ ተጉዛለች። መንገዱ የሚመራው በመደመር ፍልስፍና ነው። የዕድገት ጉዞው በማሻሻያ፣ በጽናት እና በሚላኩ ውጤቶች የተገለጠ ሆኗል። ኢትዮጵያ ወደ ፊት ስትመለከት፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ የተመዘገቡ በርካታ መሰናክሎች አልፋ ያስመዘገበችው ዕድገት አጓጊ ነው።
ያሳካቻቸው ውጤቶች መቻሏን አረጋግጠዋል። ዕድገቱ መሰረት ሰፊ፣ ጥልቅ፣ ዘርፈ-ብዙ እና ሁሉን አቀፍ ሆኖ ለትውልድ እንዲተርፍ ግስጋሴውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የመደመርን ጥሪ ይቀበሉ!
በአንድነት እንነሣ፤ አብረን እንሥራ እና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ጠንካራ እና የጋራ የሆነ ብሩህ የወደፊት ሕይወታችንን በጋራ እንቅረጽ።