በአዲስ አበባ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ሀገር በቀል እና ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ፣ የለውጡ መንግስት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በፖሊሲ ደረጃ ቀርጾ ተግባራዊ በማድረጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ግቡን እውን ማድረግ ችሏል፡፡
በ2018 ዓ.ም ይህንን ሀገራዊ ስኬት ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማከናወን በሀገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
ይህንን ግብ ማሳካት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በየካ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት የግብአት አቅርቦትና የችግኝ ጣቢያ ባለሙያ የሆኑት ስንታየሁ ግርማ፤ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በፈረንሳይ የሃ የችግኝ ጣቢያ ለዘንድሮው የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚውሉ 150ሺህ የሚሆኑ ሀገር በቀል፣ የውበትና የፍራፍሬ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
እየተዘጋጁ ካሉ የሀገር በቀል የእጽዋት ዝርያዎች መካከል ወይራ እና ብርብራ ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ ከፍራፍሬ ዝርያዎች ደግሞ ካዝሚር እና አቮካዶ በስፋት እየተዘጋጁ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
ይህ የችግኝ ዝግጅት ስራ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት ከመደገፍ ባለፈ፣ ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ የሚውሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በማካተት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በጣቢያው ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለተከላ የሚሆኑ የፍራፍሬና ሀገር በቀል ችግኞችን ጨምሮ ሌሎች ዝርያ ያላቸው ችግኞች እያዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሶስኒ ችግኝ ጣቢያ አስተባባሪ አበበች መካ ናቸው።
በዚህም በጣቢያው ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ችግኞች ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ችግኞች ፍሬያማ እንዲሆኑ ጣቢያው ለችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ቦታዎች አያያዝ፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ሲሳይ አጥናፉ፤ ለዘንድሮው የክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስድስት ሚሊየን ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመዲናዋ በሚገኙ የችግኝ ጣቢያዎች ለተከላው የሚያስፈልጉ የሀገር በቀል እና የፍራፍሬ ችግኞች በልዩ ትኩረት በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ እና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስተላለፍ የሚያስችል መሠረት የጣለ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።