የፍትህ ስርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ ስርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው
አሶሳ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦የፍትህ ስርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
4ኛው ሀገር አቀፍ የሰነድ ማረጋገጥ እና ምዝገባ የጋራ ምክክር ጉባኤ "ዲጂታል የሰነድ ማረጋገጥ እና መመዝገብ አገልግሎት ለተምሳሌት ሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ እንደተናገሩት፤ የፍትህ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ዲጂታል 2030ን ተግባራዊ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት የጀመረው ዲጂታል የአገልግሎት አሰጣጥ የፍትህ ስርዓቱን በማዘመን የዜጎችን ህጋዊ የንብረት እና ሰነድ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የዲጂታል አገልግሎት ዜጎች ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ፣ ታማኝ እና ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ በመሆን ለፍትህ ስርዓቱ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሀሚድ ኪኒሶ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ የሰነድ ማረጋገጥ እና መመዝገብ ወጥ እና ሀገራዊ የመረጃ ቋት እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የዲጂታል የሰነድ ምዝገባ እና ማረጋገጥ ከተጀመረ ወዲህ የአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻሉንና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሰነዶች ማረጋገጥ እና ምዝገባ ከዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን የዜጎችን ህይወት የሚያቃልል እና ዜጎች አስተማማኝ የሰነድ ባለቤት እንዲሆኑ ያግዛል ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ ናቸው።
አገልግሎቱ የዜጎችን እርካታ የሚጨምር እና በተቋሙ ላይ እምነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ በመሆኑ የዲጂታል አገልግሎትን የበለጠ ማስፋት ይገባል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትህ ቢሮ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች እንዲሁም የሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ አመራሮች ተገኝተዋል።