በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም መንግሥት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አክብረን እየሰራን ነው- የነዳጅ ማደያዎች - ኢዜአ አማርኛ
በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም መንግሥት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አክብረን እየሰራን ነው- የነዳጅ ማደያዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትና ዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም መንግሥት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አክብረው እየሰሩ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የነዳጅ ማደያዎች ገለጹ።
አሽከርካሪዎች በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመውን የነዳጅ ችግር በመረዳት ነዳጅን በቁጠባ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ጦርነትና አለመረጋጋት ምክንያት የነዳጅ አቅርቦት ችግር በሀገርና በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳያሳድርና በፍትሐዊነት ለመምራት የሚያስችል የቅድሚያ አሰጣጥ ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም የነዳጅ አቅርቦት የሚያገኙ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣ ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣ ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች እና ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ የሚያገኙ ናቸው።
በተጨማሪም የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች፣ ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮች፣ የከተማና ሀገር አቀፍ የብዙሃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም በናፍጣ የሚሰሩ ሌሎች ለህብረተሰብ ግልጋሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ የቅድሚያ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራርን የሚጠይቅ ነው።
ይህን መመሪያና ውሳኔ አክብረው እየሰሩ ስለመሆኑ ኢዜአ በመዲናዋ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎችን ተዘዋውሮ በመመልከት የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሯል።
መንግሥት የነዳጅ አቅርቦት ችግር በሀገርና በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ጫና እንዳያሳድርና በፍትሐዊነት ለመምራት ተግባራዊ እንዲሆን ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አክብረው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የነዳጅ ማደያዎች መካከል የአሮጌው ቄራ ቶታል ማደያ ሱፐርቫይዘር ይርጋ ኪዳነማርያም እንደገለጹት፤ መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
በተለይም የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው በተሰጠው መመሪያ መሰረት ቅድሚያ በመስጠት በኩል ሀላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው የሰባራ ባቡር ቶታል ነዳጅ ማደያ ሱፐርቫይዘር ሀብተዮሃንስ ግርማ እንደገለጹት፤ ቅድሚያ መስጠት ላለባቸው ተሸከርካሪዎች ቅድሚያ በመስጠት እያስተናገዱ ናቸው።
በዚህም ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ለአምቡላንሶች ለእሳት አደጋ መኪኖችን ጨምሮ ሌሎችም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተሸከርካሪዎችን በማስቀደም አገልግሎቱን በተገቢው ሁኔታ እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአራዳ ጊዮርጊስ ቶታል ነዳጅ ማደያ ሱፐርቫይዘር ቢንያም ክፍሌ ናቸው፡፡
አሽከርካሪዎች በበኩላችው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመውን የነዳጅ ችግር በመረዳት ነዳጅን በቁጠባ እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል።
አሽከርካሪ መዋል አየለ፤ ነዳጅ በማደያዎች በወረፋቸው መሰረት ያለምንም ችግር እያገኙና እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው አሽከርካሪ አብይ ሻንቆ በበኩላቸው፤ የነዳጅ እጥረትን ተከትሎ ሞተር በማጥፋት ጭምር የነዳጅ ቁጠባ እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ነዳጅን በቁጠባ በመጠቀም ላይ መሆናቸውን በመግለጽ በነዳጅ ማደያዎችም ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ተሸከርካሪዎች ቅድሚያ እየተሰጣቸው እየተስተናገዱ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አሽከርካሪ አንድነት አሸናፊ ናቸው።
ነዳጅን በቁጠባ በመጠቀምና በነዳጅ ማደያዎች ወረፋውን በመጠበቅ ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም አሽከርካሪዎች ተናግረዋል።