ቀጥታ፡

ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት ትኩረት ተደርጓል

ሰመራ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ በሠመራ ከተማ  እየተካሔደ ነው።


 

በጤና ሚኒስቴር የጤና ስርዓት ፍትሃዊነት እና አመራር ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ገሙ ቲሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤የጤና አገልግሎትን ማሳደግ ዘርፉን ለመለወጥ ከተቀመጡት የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ዋነኛው ነው።

በዚሁ መሰረትም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎት በመስጠት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሒደት  የተለያዩ የጤና አገልግሎቶችን  ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራትን  ከ2018 ዓ.ም  ጀምሮ መንግስት እያስቀጠላቸው መሆኑን ነው ያስረዱት።

የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመር ኑር በበኩላቸው፤ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎት የአርብቶ አደሩ ማሕበረሰብ ጤናውን እንዲጠብቅ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል።


 

የህክምና አገልግሎቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ፣ የእናቶችና ህፃናት ጤናን ለመጠበቅ እና የክትባት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል።

በክልሉ በሚሰጠው ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት ከ370 ሺህ በላይ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ  ናቸው።


 

ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎቱ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ሲሰጥ የቆየ መሆኑንም አስታውሰዋል። የምክክር መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም