ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለህገ-ወጥ ግብይት ሊውል የነበረ ከ80 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተያዘ

አርባምንጭ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለህገ-ወጥ ግብይት ሊውል የነበረ ከ80 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ሲያዝ ስምንት ማደያዎችም ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው መታሸጋቸውን የክልሉ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ እንዲሁም መንግሥት የሚከተላቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች በተመለከተ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)  ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።

የችግሩን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገና መፍትሄዎችን ያገናዘበ አሰራር መከተልና መፍትሄውን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን ከተቀመጠው አሰራር ውጭ ግብይት እንዳይኖር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ ነው።

በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ሲሆን ከዚህ አሰራር ውጭ ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል በመደረግ ላይ ይገኛል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን፤ አሰራሩን ተግባራዊ የማድረግና ቁጥጥሩን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ለህገ-ወጥ ግብይት ሊውል የነበረ ከ88 ሺህ 24 ሊትር በላይ ናፍጣና ቤንዚን ከወንጀሉ ተጠርጣሪ 39 ግለሰቦች ጋር መያዙን ጠቅሰዋል።

በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር ስምንት ማደያዎችም ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው መታሸጋቸውን ገልጸው ከህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትና ስርጭት ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ጥቆማ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣው የነዳጅ ቁጠባ መመሪያ በክልሉ ባሉ ማደያዎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰው በከፍተኛ የመንግስት ድጎማ እየመጣ ያለው ነዳጅ በፍትሃዊ መንገድ እንዲሰራጭ የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም