የኢትዮጵያ የከተማና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስኬቶች በአርዓያነት የሚወሰዱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የከተማና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስኬቶች በአርዓያነት የሚወሰዱ ናቸው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የከተማና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ የልማት ስኬቶች የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት በአርዓያነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋዜጠኞች ገለጹ።
የኢትዮጵያ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስኬቶች በሀገር ገጽታ በመገንባት የከተማ ነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሻሻል አስተማማኝ ምኅዳር ፈጥረዋል።
በአዲስ አበባ ተጀምሮ በበርካታ ከተሞች ተግባራዊ የተደረገው የኮሪደር ልማትም የንግድና ቱሪዝም እንቅስቃሴን በማሳለጥ ዘመናዊ፣ ውብና ፅዱ ከተሞችን እየፈጠረ ይገኛል።
በሌላ መልኩም ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ተግባራዊ ያደረገችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የልማት አቅጣጫም ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው።
የአረንጓዴ አሻራና የታዳሽ ኃይል፣ የበጋና የመኸር ወቅት የሰብል ምርታማነት፣ ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄና የአካባቢ ጥበቃ የልማት መርሃ ግብሮች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ አብነቶች ናቸው።
በተለይም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያን የአፍሪካ ሳንባ የማድረግ ትልም ያስመዘገበው ስኬት የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን በመሸፈን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከተ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና እየተቸረው የሚገኝ አስደናቂ የልማት ትልም ሆኗል።
የደቡብ ሱዳን፣ ዑጋንዳና ቡሩንዲ ጋዜጠኞች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በከተማ ልማትና በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም አስደናቂ የልማት ጉዞ ላይ መሆኗን መስክረዋል።
የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኛ አይዛክ ዱዶሩ አማኑኤል፤ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት አጋጣሚ አዲስ አበባ የሚታይና የሚጨበጥ የልማት እንቅስቃሴ ያላት ከተማ መሆኗን መገንዘቡን ገልጿል።
ይህም በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ፈጣንና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥኑ የልማት መርሃ ግብሮች እየተገነቡ እንደሚገኝ ማሳያ ነው ብሏል።
የቡሩንዲ ጋዜጠኛው ሜሻ ኬንዲ ኩምንጋም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የልማት መርሃ ግብሮች የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት ትምህርት የሚቀሰምበትና አስደናቂ የአመራር ቁርጠኝነት ውጤት መሆኑን ተናግሯል።
የዑጋንዳ ጋዜጠኛ ኮሙ ዴኒስ በበኩሉ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ የልማት መርሃ ግብሮች ጥራትን ከውበት ያሰናሰሉ አስደናቂ የልማት ውጤቶች መሆናቸውን ገልጿል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የታዳሽ ኃይል ልማት መርሃ ግብሮች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ዓለም አቀፍ የልማት ውጤቶች እንደሆኑ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢኮኖሚ ግንባታም የተሳለጠ ዕድገት የሰፈነባት አፍሪካን እውን ለማድረግ በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አንስቷል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የአካባቢ መራቆትን በደን በመሸፈን የተፈጥሮ ሚዛንን የሚያስጠብቅ ወሳኝ የልማት እርምጃ መሆኑን አብራርቷል፡፡