ቀጥታ፡

መጋቢት 24 ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የልዕልና ምዕራፍ ያሸጋገረ አዲስ የተስፋ አድማስ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018 (ኢዜአ)፦ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ የታሪክ አውድ ውስጥ አዲስ ትርጉምና ጽኑ ቃል-ኪዳን ተላብሶ ብቅ ያለ፣ ለሀገራችንና ለሕዝቦቿም አዲስ የተስፋ አድማስን የፈነጠቀ ክስተት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

ዕለቱ ኢትዮጵያን ተብትቦ ይዞ ከነበረው ውስብስብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቅርቃር አውጥቶ ወደ ብሩህ መጻኢ ዕድል ለማሸጋገር የተገባ ታላቅ የትውልድ ውል ሆኖ መመዝገቡን አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ከመጋቢት 2010 እስከ መጋቢት 2018 ዓ.ም ባሉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የጊዜ ጉዞ ውስጥ፣ ሀገራችን ያስመዘገበቻቸው ድሎች፣ የተሻገረቻቸው ክፉ ፈተናዎችና የገነባቻቸው ተጨባጭ እውነታዎች ኢትዮጵያን ከነበረችበት የውድቀት ስጋት ታድገው ወደ ላቀ የልዕልና ምዕራፍ ያሸጋገሩ መሆናቸውን አገልግሎቱ ገልጿል።

ይህ የትንሣኤ ጉዞ በፈተና እቶን ውስጥ አልፎ የነጠረ፣ በጽናት የታነጸና የኢትዮጵያን የማይበገር ማንነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዳግም ያስመሰከረ የታሪክ አሻራ መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል።

የዛሬው የፖለቲካ ምኅዳራችን አስኳል የተቀዳው ከዚሁ ከመጋቢት 24ቱ የታሪክ ብርሃን መሆኑን የጠቀሰው አገልግሎቱ፤ የሐሳብ ልዩነትን በጸጋ የሚቀበል፣ የመሐልና የዳር ፖለቲካዊ ቅራኔዎችን በማክሰም ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ያጸና፣ እንዲሁም ከፋፋይና ነጠላ ትርክቶችን በማርገብ የወል ሀገራዊ እሴቶችን የሚያሰርጽ ሥርዓት ዕውን መሆኑን ገልጿል።

ብሔራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን የሚያስቀድም፣ ዜጋ-ተኮር ዲፕሎማሲን የሚከተልና ለጎረቤት ሀገራት ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጥ የፖለቲካ ሥነ-ምኅዳር መሠረቱ የተጣለውም በዚህ ወቅት እንደነበርና በአሁኑ ወቅትም አካታች ሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ የማስፈን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርቷል።

የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸውን በተግባር እየተለማመዱ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በነፃነትና በሕግ አግባብ ራሳቸውን ለውድድር እያቀረቡ እንደሚገኙ በመግለጫው ተመልክቷል።

መንግስት አካታች የፖለቲካ ስርዓት እንዲሰፍን በወሰደው ብስለት የተሞላበት እርምጃ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ከካቢኔ ጀምሮ በየደረጃው ሥልጣን እያጋራና ሀገር በጋራ የመምራት ዕድል እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቀሰው አገልግሎቱ፤ ይህም ኢትዮጵያውያን በለውጡ ብሥራት አማካኝነት ከመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ መተባበር የዲሞክራሲ ልምምድ መሸጋገራቸውን በግልጽ ያሳያል ብሏል።

መጋቢት 24 የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስብራት የታከመበትና አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የተጀመረበት መሆኑን ያመለከተው አገልግሎቱ፤ የለውጡ መንግሥት ኢኮኖሚው ተጋርጦበት ከነበረው አደገኛ ቅርቃር በመበጣጠስ ኢትዮጵያን አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ማድረግ መቻሉን ገልጿል።

አዳዲስ የንግድ ብድሮችን ከመውሰድ በመቆጠብና የነበሩትንም በድርድር ወደ ተራዘመ የክፍያ ጊዜ በመቀየር ኢኮኖሚውን ከውድቀት መታደጉንና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች አማካኝነት የሀገሪቱን ጸጋዎች በላቀ ደረጃ መጠቀም መጀመሩን በመግለጫው አስታውቋል።

እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ካጋጠሟቸው መዋቅራዊና የአፈጻጸም ችግሮች ወጥተው ዓለምን ባስደመመ ተአምር ለምርቃት መብቃታቸውንና ኢትዮጵያ በአዲስ የኢኮኖሚ ምሕዋር ውስጥ መግባቷን ለዓለም ማሳየቷ ተገልጿል።

ይህም ሀገሪቱ ያላትን ታሪካዊ የነፃነት ቀንዲልነት ከኢኮኖሚ ልዕልና ጋር አጣምሮ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ተሰሚነቷ እንዲጎላ ማድረጉን የገለጸው አገልግሎቱ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ በየሳምንቱ የታላላቅ ሀገራት መሪዎችን የምታስተናግድና ዲፕሎማሲዋ ከተከላካይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት ያደገባት ኃያል ሀገር መሆኗን አስታውቋል።

በተመሳሳይ መልኩ መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ከተሞች ዳግም የተወለዱበት መነሻ ሆኖ ማገልገሉንና በኮሪደር ልማት አማካኝነት ከተሞች አዲስ ገጽታን መላበሳቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

ማኅበራዊ መስተጋብር ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲጠናከር፣ ብዝኃነት የሀገር ጌጥና አንድነት ደግሞ የሀገር ዐቅም እንዲሆን መደረጉን የጠቀሰው አገልግሎቱ፤ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን በጋራ የመጋፈጥ ባህል ጎልቶ መታየቱንና ለተጎዱ ወገኖች የተደረገው ሀገራዊ ድጋፍ የዚሁ ጽኑ አንድነት ማሳያ መሆኑን አገልግሎቱ አብራርቷል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በኃይልና በምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ አስደማሚ ስኬቶችን ማስመዝገቧንና በታዳሽ ኃይል ልማት ለዓለም አብነት መሆን መቻሏንም ገልጿል።

ምንም እንኳን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ጉዞዋን ለማዘግየት ቢሞክሩም፣ ኢትዮጵያ አሁንም በአስተማማኝ የፖሊሲ አቅጣጫ ላይ እንደምትገኝና አዲሲቷ የተስፋ አድማስ ሆና እንደምትቀጥል በመግለጫው ተመልክቷል።

ዛሬ ላይ የለውጡን መሠረት ከማስፋትና ከማጽናት ወደ ማላቅ የተሸጋገረችው ኢትዮጵያ፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌትነቷን በተግባር እንደምታውጅ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም