ቀጥታ፡

የሲዳማ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ ነው

ሃዋሳ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ የሲዳማ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ እየሰጠ መሆኑን  የይርጋለም ከተማ ተገልጋዮች ገለጹ፡፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቴክኖሎጂ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን አገልግሎቶች በአንድ ዲጂታል ሥርዓት በማቀናጀት፣ ደንበኞች እንደ መንጃ ፈቃድ፣ መታወቂያ እና የባንክ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላል። 

በሲዳማ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎትም 17 ተቋማት የገቡ ሲሆን ከ74 በላይ አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የማእከሉ ተገልጋዮች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በቴክኖሎጂ የታገዘው የማእከሉ አገልግሎት ጊዜ፣ ወጪንና እንግልት የቀነሰና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄን የሰጠ ነው፡፡


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የይርጋለም ከተማ ነዋሪው አቶ ከበደ አመሎ የመጡበትን ጉዳይ በአስር ደቂቃ ውስጥ መፈጸማቸውን ጠቅሰው ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር የተንዛዛ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

አገልግሎቱ በዲጂታል የታገዘ መሆኑና የተለያዩ ተቋማት በአንድ ቦታ መገኘታቸው የተገልጋዩን እንግልት ለመቀነስና  ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

የማእከሉ አገልግሎት የተገልጋይ እርካታን ከማሳደግ ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በመንግስትና ህዝብ መካከልም መተማመን ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

ሌላኛው ተገልጋይ አቶ ዎማ ጋቢሶ በበኩላቸው ውክልና ለመስጠት ወደ ማእከሉ መምጣታቸውን ጠቅሰው በተቋሙ የተፈጠረው አዲስ የስራ እሳቤ የተገልጋዩን ጊዜ፣ ወጪና እንግልት ከመቀነስ ባለፈ በእውቀት እንዲገለገል አስችሏል ብለዋል፡፡


 

ስለሚያገኙት አገልግሎት የህግ ድጋፍ ጭምር ማግኘታቸውን ጠቅሰው አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑና የተለያዩ ተቋማት በአንድ ላይ መኖራቸው አገልግሎቱን ቀልጣፋ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

በማእከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ፍትሃዊና ከዚህ ቀደም ለሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄን ያመላከተ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በማእከሉ የሚሰጠው አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን የገለጹት ወይዘሮ መታሰቢያ አለማየሁ በበኩላቸው በአገልግሎት አሰጣጡ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

የማእከሉ መከፈት ከዚህ ቀደም ረጅም ጊዜ ወስዶ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በ15 ደቂቃ ውስጥ መፈጸም በመቻላቸው ጊዜ፣ ወጪና እንግልትን ቀንሶላቸዋል፡፡

የሲዳማ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ እንግዳየሁ ዘውዴ በማእከሉ 17 ተቋማት መኖራቸውንና 74 አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ከ35 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች አገልግሎት መሰጠቱን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ የተገልጋዮች እርካታን  ለመፈተሽ በተደረገው  የዳሰሳ  ጥናት ተግባሩ  ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት ከዚህ ቀደም በአገልግሎቱ ዘርፍ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ በመንግስትና ህዝብ መካከል መተማመን እንዲፈጠር እያስቻለ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም በክልሉ በሚገኙ ሰባት ከተማ አስተዳደሮችና በሃዋሳ ከተማ ተጨማሪ ማዕከል በማቋቋም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት መስከረም 15/2018 ዓ.ም ተመርቆ በይፋ ወደ አገልግሎት መግባቱ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም