ኢትዮጵያ በፊፋ የዓለም አገራት ወርሃዊ ደረጃ ደረጃዋን አሻሻለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በፊፋ የዓለም አገራት ወርሃዊ ደረጃ ደረጃዋን አሻሻለች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በየወሩ ይፋ በሚያደርገው የአገራት እግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ ሶስት ደረጃዎችን አሻሽላለች።
ፊፋ የእ.አ.አ ማርች ወር 2025 የሀገራት ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃን ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ከነበረችበት 147ኛ ደረጃ ወደ 144ኛ ከፍ ብላለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን በድምር ውጤት 4 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ምድብ ማጣሪያው ማለፉ ለደረጃው መሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል።
ሞሮኮ ከዓለም ስምንተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዛለች።
ሴኔጋል 14ኛ፣ ናይጄሪያ 26ኛ፣ አልጄሪያ 28ኛ፣ ግብጽ 29ኛ፣ ኮትዲቯር 34ኛ፣ ቱኒዚያ 44ኛ እና ካሜሮን 45ኛ የተሻለ ደረጃ ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ናቸው።
ለ23ኛው የዓለም ዋንጫ ያለፈችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደረጃውን ከ48ኛ ወደ 46ኛ ከፍ አድርጋለች።
ፈረንሳይ በፊፋ ወርሃዊ የሀገራተ ደረጃ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች። ስፔን ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የወቅቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ አርጀንቲና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
እንግሊዝ፣ ፖርቹጋል፣ ብራዚል እና ኔዘርላንድስ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ከ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ውጪ የሆነችው ጣልያን 12ኛ ደረጃን ይዛለች።
የአውሮፓዋ ሳን ማሪኖ የመጨረሻው 211ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የቡድን ጥንካሬ፣ የሚደረገው ጨዋታ ያለው ወሳኝነት፣ የጨዋታ ውጤትና ከጨዋታ በፊት የሚጠበቅ ውጤት ፊፋ የሀገራትን የእግር ኳስ ደረጃ የሚለካባቸው መመዘኛዎች ናቸው።