የለውጡ መንግስት ያስመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ በተግባር ያስመሰከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ መንግስት ያስመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ በተግባር ያስመሰከረ ነው
አሶሳ፤ መጋቢት 24/2018 (ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግስት ውስብስብ ችግሮችን በማለፍ ያስመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያን ብልጽግና ጉዞ በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ።
የለውጡ መንግሥት ሀገራዊ ኃላፊነት የተረከበበትን 8ኛ ዓመት አስመልክቶ በአሶሳ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሠልፍ ተካሂዷል።
በዕለቱ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያበስሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ውጤታማ ተግባር ፈጽሟል።
የለውጡ መንግስት ውስብስብ ችግሮችን በማለፍ ያስመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ በተግባር አስመስክሯል ነው ያሉት።
ባለፉት ስምንት ዓመታት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለውጡ ያስገኘውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በፖለቲካው ኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በለውጡ መንግስት ያገኘውን ሰላምና ልማት በማስቀጠል ኢትዮጵያ ለያዘችው የብልጽግና ጉዞ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አብዱልከሪም አብዱራሂም በበኩላቸው የለውጡ መንግስት ከተሞችን ለማዘመን በጀመረው የኮሪደር ልማት የአሶሳ ከተማን ጨምሮ ትልልቅ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፉ አስተያየት ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ሲቱ አልበሽር እና ደሳለኝ አሳዬ እንደተናገሩት፤ የለውጡ መንግስት እያከናወናቸው የሚገኙት የልማት ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትና የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ማሳደጋቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም መንግስት የጀመራቸው የልማት ስራዎችን በመደገፍ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።