መንግስት ኢትዮጵያን የሚመስሉ ጠንካራ ተቋማት ለመገንባት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ኢትዮጵያን የሚመስሉ ጠንካራ ተቋማት ለመገንባት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው
ጅማ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ በለውጡ ዓመታት መንግስት ኢትዮጵያን የሚመስሉ ጠንካራ ተቋማት ለመገንባት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን፤ መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተቋማት መገንባት ሀገርን መገንባት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፅ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህንም ታሳቢ ያደረገ ስራን በመስራትም ኢትዮጵያን የሚመስሉ ተቋማትን ለመገንባት መቻሉን አስረድተዋል።
በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገርን የሚመስሉ የፀጥታና የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባታቸውን የቦረና እና የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናግረዋል።
የቦረና ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በፍቃዱ ጨመረ (ዶ/ር) ሀገርን የመሠሉ ተቋማት መገንባታቸው ኢትዮጵያን ከፍ አድርጓታል ብለዋል።
ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያን የሚመጥኑ እና ሀገርን የሚመስሉ ተቋማት እንዲገነቡ የብዙዎች ጥያቄ እና ፍላጎት እንደነበር አስታውሰዋል።
ሆኖም ከለውጡ በኋላ ወዲያውኑ የተቋማት ግንባታ እና የሪፎርም ስራ መጀመሩ ዛሬ ላይ ሀገርን የሚወክሉ ተቋማትን እንድናይ አስችሎናል ነው ያሉት።
ተቋማት በዚህ መልኩ መገንባታቸው ፅኑ እና ቀጣይነት ያላቸው እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል።
ለአብነትም የፀጥታ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትኩረት የተሰራባቸው መሆኑን ጠቁመው እነዚህ ተቋማት ለዓመታት የዜጎች ጥያቄ ምላሽ የሰጡ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን ጥሩነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ እየተገነቡ ያሉ ተቋማት ነገ የበለጠ ከፍ ያለች ሀገር እንድናይ ያስችለናል ብለዋል።
መጀመሪያ ጠቃሚ ሀሳብ ሲኖር እና በወረቀት ላይ ሲሰፍር ሀሳቡን የሚሸከም ተቋም ያስፈልግ ነበር ያሉት ሰለሞን ጥሩነህ (ዶ/ር) ባለፉት የለውጥ ዓመታት አይሆንም ያልነው ተቋም ሆኖ ሀገርን መስሎ ተገንብቶ ተመልክተናል ነው ያሉት።
ለአብነት ከሚጠቀሱ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ቦርዱ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የተገነባ ተቋም መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በዚህ መልኩ መገንባቱ በታሪክ ከምናውቀው በተቃራኒ ከጫና ተላቆ እንዲሰራ እንዳስቻለውም አስረድተዋል።
የፍትህ ተቋማት በተመሳሳይ ህግን መሠረት ያደረገ እና የአንድ አካል ወገንተኝነት የማይታይባቸው ለማድረግ የተሄደበት መንገድ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚሁ በተጨማሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ወቅታዊ ቁመና ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ህገ-መንግስቱን መሠረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ እና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስቀድም ነው በማለት ገልፀዋል።
ተቋማቱ በቴክኖሎጂ የታገዙ እና ዘመናዊ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለው ስራም በሂደት ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልፀው ከፊታችን ላለው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቦርዱ በዲጂታል ስርዓት እየታገዘ መሆኑንም በምሳሌነት ጠቅሰው አድንቀዋል።
ተቋማትን አሁንም ይበልጥ በቴክኖሎጂ ማዘመን አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
መሰል ተቋማትን ይበልጥ በመገንባት ጠንካራ መሠረት ያለው ተሻጋሪ የዴሞክራሲ ስርዓትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አክለዋል።