መጋቢት 24 ዴሞክራሲ ወደ ፊት የመጣበት እና የመደመር ሀሳብ ያሸነፈበት ዕለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
መጋቢት 24 ዴሞክራሲ ወደ ፊት የመጣበት እና የመደመር ሀሳብ ያሸነፈበት ዕለት ነው
ጅማ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ መጋቢት 24 ዴሞክራሲ ወደ ፊት የመጣበት እና የመደመር ሀሳብ ያሸነፈበት ዕለት ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ ገለጹ።
በጅማ ከተማ የሀገራዊ ለውጡን 8ኛ ዓመት አስመልክቶ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ነመራ፤ ቀኑ ኢትዮጵያ በመሳሪያ ሳይሆን በሀሳብ አሸናፊነት የምትተዳደር መሆኗን ለአለም ያሳየንበት ነው ብለዋል።
ኃላፊው በንግግራቸው ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራትና የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ መላክ መቻሉን እንደ ትልቅ ስኬት ጠቅሰዋል።
ከለውጡ በኋላ የገጠሙንን ፈተናዎች ወደ ዕድል በመቀየር በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ ነመራ፣ ጫናዎችን በመቋቋም ጠንካራ ስራዎች የተሰሩበት መሆኑን ተናግረዋል።
ቀጣይ ትኩረትም የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባትና ማህበራዊ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፣ መጋቢት 24 ብሔር ብሔረሰቦች ያሸነፉበት እና አዲስ የለውጥ ምዕራፍ የተጀመረበት በመሆኑ ሁሌም በታሪክ ሲታወስ እንደሚኖር ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በምዕራብ ወለጋ ዞን የሀገራዊ ለውጡን 8ኛ ዓመት አስመልክቶ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፋ እንደተናገሩት፤ መጋቢት 24 በዞኑ የልማት ድል እንዲመዘገብ ያደረገ ዕለት ነው።
አካባቢው በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በነበረበት ወቅት የዞኑ ነዋሪ ሰላምና ልማት ፈላጊ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም በለውጡ የተመዘገቡ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች እንዳይደናቀፉ እያንዳንዱ ነዋሪ አካባቢውን በመጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በጊምቢ ከተማ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት ነዋሪዎችም በለውጡ ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል።
የመጋቢት 24ን የስኬት ጉዞ ምክንያት በማድረግ በጊምቢ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የታደሙ ነዋሪዎች፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን መስክረዋል።
አቶ ቡሳ ገርማማ እና አቶ ወሰኑ ተርፋሳ "ባለፉት ዓመታት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በስፋትና በጥራት ተሰርተዋል፤ በቀጣይም የታቀዱ የልማት ስራዎች ግባቸውን እንዲመቱ የበኩላችንን እንወጣለን" ብለዋል።
በዞኑ በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፣ የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር ከምንጊዜውም በላይ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።