የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦በሀገራዊ የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአፈር ለምነትን በማሳደግና ምርትና ምርታማነትን በማረጋገጥ ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያበረከተ መሆኑን የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ገለፀ።
መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበትና ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበት ዕለት ነው፡፡ ይህንኑ ለውጥ ወደ ተግባር ከቀየሩትና የለውጡ ትሩፋት ተብለው ከሚጠቀሱ ስኬቶች መካከል ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም. የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዋና ግቡ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ማሳደግ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ አካባቢን መፍጠር መሆኑ ይታወቃል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከ23 ነጥብ 6 በመቶ በላይ ማድረስ ማስቻሉ ከንቅናቄው ስኬቶች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ሰፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እያስገኘ ሲሆን የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ከማስገኘቱም በላይ፣ ለጎረቤት ሀገራትም ችግኞችን በማካፈል ቀጠናዊ ትስስርን ማጠናከር አስችሏል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግስት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሰጠው ትኩረትም የተፈጥሮ ሃብቶችን በማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማበርከት ያስቻለ ውጤት ተገኝቷል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአካባቢ ስነ-ምህዳርን በመጠበቅና የደን ሽፋንን በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በዚህም በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በተደረገ ጥናት እስካሁን ከተተከለው 48 ቢሊዮን ችግኝ 30 በመቶ የሚሆነውን በአባይ ተፋሰስ የሚገኙ ወረዳዎች ላይ መተከሉን ያሳያል ነው ያሉት።
እንዲሁም በአዋሽ ተፋሰስ እና ስምጥ ሸለቆ ውስጥም ተመሳሳይ ጥናት መካሄዱን ገልፀው፤ የመሬቱ የደን ሽፋን በማደጉ የከርሰ ምድር ውሃው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር መቻሉን ጥናቱ ያመለክታል ብለዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፋኖስ መኮንን በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በማሳደግ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ ከተጀመረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተተከለው ችግኝ ተመናምኖ የነበረው የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በዚህም አሁን ላይ የደን ሽፋኑን ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ባለፈው ዓመት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል።
መርሀ-ግብሩ በኢትዮጵያ ያለውን የደን ሽፋን በእጅጉ ከማሳደጉ ባሻገር በአትክልትና ፍራፍሬ ምርትና ምርታማነት በመጨመር ከህዝቡ ተጠቃሚነት ባሻገር ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው ብለዋል።