መጋቢት 24 በየዘርፉ ለተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች መሠረት የተጣለበት ዕለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
መጋቢት 24 በየዘርፉ ለተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች መሠረት የተጣለበት ዕለት ነው
ማያ ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦መጋቢት 24 በየዘርፉ ለተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች መሠረት የተጣለበት ዕለት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ሃላፊ መሰረት አሰፋ ተናገሩ።
የሀገራዊ ለውጡን 8ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ማያ ከተማ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በከተማ አስተዳደሩ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ በየደረጃው የሚገኙ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎችም 'የተገኘውን ለውጥ እናስቀጥላለን'፣ 'መጋቢት 24 የለውጥና የኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የተጣለበት እለት ነው'፣ 'መጋቢት 24 የብርሃን ጉዞ መሰረት ነው!!!' የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡
በዕለቱ መልዕክት ያስተላለፉት የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ሃላፊ መሰረት አሰፋ እንደገለፁት፤ መጋቢት 24 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ለማሻገር ስልጣን የተረከቡበት ቀን ነው።
የለውጡ መንግስት ፈተናዎችን በድል እየተሻገረ ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉም ተናግረዋል።
ለውጡ በክልሉ ሰላምና ልማትን በማጎልበት ህብረተሰቡ በልማት ስራ ላይ እንዲሰማራና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ማድረጉንም አብራርተዋል።
በተለያዩ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎችም የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያረጋግጡ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ በበኩላቸው፤ መጋቢት 24 በሀገሪቱ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀበት ቀን ነው ብለዋል።
ለውጡን ለመደገፍ ህዝቡ በነቂስ በመውጣቱ ምስጋና አቅርበው፤ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ እንዲያስቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።