የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል አብሮነት እንዲጠናከር እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል አብሮነት እንዲጠናከር እያገዘ ነው
ሐረር ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል መካሔዱ ክልሎች ያላቸውን ባሕልና እሴት ለማስተዋወቅና አብሮነትን ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተገለጸ።
23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 19ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል "የባህል ስፖርቶች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ በሐረሪ ክልል እየተካሄደ ይገኛል።
በውድድሩና ፌስቲቫሉ በ11 የስፖርት ዓይነቶች ከ1ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች እየተሳተፉ ይገኛሉ ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተሳታፊዎች የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የእርስ በእርስ ትውውቅን ለማሳደግና የባህል ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጣው ፍጹም ገላና የባህል ውድድሩና ፌስቲቫሉ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና ትውፊት እንድናውቅ ረድቶናል ሲል አመልክቷል።
በተለይም የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነት ይበልጥ እንዲጎለብት ያደርጋል ብሏል።
ውድድሩና ፌስቲቫሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አኩሪ ባህሎቻቸውን ለማስተዋወቅ ምቹ ዕድል ፈጥሯል ያለችው ደግሞ ከአማራ ክልል የባህል ስፖርት ተሳታፊዋ ስንዱ መላዕክ ናት።
በፌስቲቫሉ የእርስ በርስ የባህል ልውውጥ እያደረጉ እንደሚገኙና ይህም አብሮነትን ከማጠናከሩ ባለፈ ለሰላም ግንባታ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የምትናገረው።
ከኦሮሚያ ክልል ውድድሩና ፌስቲቫሉ ላይ ለመሳተፍ የመጣው ወጣት በላይ ደረሱ "ፌስቲቫሎችና ውድድሮቹ የማናውቃቸውን ባህላዊ ጨዋታዎች፣ እሴቶች፣ ባህልና ወጎችን ለማወቅ አስችሎናል" ነው ያለው።
የባህል ውድድሩና ፌስቲቫሉ የጋራ እሴቶችን አጉልቶ ለማውጣት፣ ወንድማማችነትን ለማጠናከርና አንዱ የሌላውን ባህል ለማወቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል የልዑካን ቡድን አባል አቶ ማዕረግ በቀለ ናቸው።
ይህም በህዝቦች መካከል ሰላም፣ አንድነትና መከባበርን በማጎልበት ረገድ ሚናው የላቀ መሆኑን አመላክተዋል።
23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 19ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል የፊታችን እሁድ ፍጻሜውን ያገኛል።