ቀጥታ፡

ቻይና ለኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፏን እንደምታጠናክር ገለጸች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ ቻይና ለኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ ከቻይና ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (CIDCA) ምክትል ሊቀመንበር ሊዩ ጁንፌንግ ጋር በቤጂንግ ከፍተኛ ደረጃ ምክክር አድርጓል።


 

የውይይቱ ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን የቆየና የጠነከረ አጋርነት ይበልጥ ማሳደግ ነው።

ውይይቱ ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን የልማት ጉዳዮች መሠረት በማድረግ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ያተኮረ ነበር።

የኢትዮጵያ ልዑክ ሀገሪቱ እያካሄደች ያለውን ኢኮኖሚያዊ ሪፎርምና የልማት አጀንዳዎችን ያብራራ ሲሆን፣ ዘላቂ ዕድገትንና መዋቅራዊ ሽግግርን ለማምጣት ቀጣይነት ያለው ትብብር አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥቷል።

የቻይና ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ሊቀመንበር ሊዩ ጁንፌንግ በበኩላቸው፣ ቻይና በዝቅተኛ ወለድ የሚሰጡ ብድሮችን፣ የቴክኒክ ድጋፎችንና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በማጠናከር ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል በድጋሚ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን የገመገሙ ሲሆን፣ በተለይም በባቡር መሠረተ ልማት፣ በግብርና፣ በዲጂታል ልማት፣ በኢንዱስትሪና በጤና ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማስፋት በሚቻልባቸው ዕድሎች ላይ ተወያይተዋል።

ሁለቱ ወገኖች ትኩረት የሰጧቸው ጉዳዮች ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዲቀየሩ ተቋማዊ ግንኙነቶችን ይበልጥ ለማሳደግና ተቀራርበው ለመስራት ተስማምተዋል።

ይህም በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን ሁለንተናዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም