ቀጥታ፡

የለውጡ መምጣት ሰው ተኮር ተግባራትን የሁሉም ህዝብና ተቋማት ሃላፊነት ለማድረግ አስችሏል

ባህር ዳር፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ ለሰው ተኮር ተግባራት ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ማስቻሉን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ንጹህ ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ ለሰው ተኮር ተግባራት የተሰጠው ትኩረት በተለይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሕል እንዲሆን አድርጓል።

ለአብነትም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በክልሉ ለተከናወነው ሰው ተኮር የበጎ አድራጎት ተግባር ከ397 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ከማሕበረሰቡ ተሰብስቦ ስራ ላይ ውሏል ነው ያሉት።

በተሰበሰበው ሀብትም ከ33ሺህ 900 በላይ የነባር ቤቶች እድሳትን ጨምሮ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አቅመ ደካማ ወገኖች አዲስ የመኖሪያ ቤት መገንባት መቻሉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከ505ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የማዕድ ማጋራት፣ የልብስና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፎች መደረጉን ጠቁመው ከ267ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎችም በየአመቱ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት።

በግብርና፣ በጤናና ሌሎች የልማት ዘርፎችም እንዲሁ በበጎ አድራጎት ላይ የተመሰረተ የሰው ተኮር ተግባራት መከናወኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም