ቀጥታ፡

በለውጡ መንግስት የተገኙ ትሩፋቶችን አጠናክረን እናስቀጥላለን

ጅማ፤ መጋቢት 24/2018(ኢዜአ)፦ በለውጡ መንግስት የተጀመሩ የልማት ስራዎችና የተገኙ ትሩፋቶችን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የለውጡ መንግስት የተመሰረተበትን 8ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በጅማ ከተማ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በሰልፉ የተሳተፉ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች የለውጡ መንግስት የጀመራቸውን ትልልቅ የልማት ስራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተጀመሩ ትልልቅ የልማት ስኬቶችን በመደገፍ ከዳር ማድረስና ኢትዮጵያን ወደሚገባት ከፍታ ማሻገር የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

የጅማ ከተማ ነዋሪ ንጋቱ ደምሴ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የለውጡ መንግስት ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ጠንካራ ትብብር የተጀመረውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ ችሏል ብለዋል።

ይህም ቀላል የማይባሉ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን በብልሀት በማለፍ የመጣ ስኬት መሆኑን ጠቁመው መሠል ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል በጋራ መቆም ያስፈልጋል ብሏል።

ወይዘሮ ሮዛ ተካ በበኩላቸው የለውጡ መንግስት ባለፉት አመታት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በተለይም የባህር በር ባለቤትነት የማግኘት ጉዳይ ከጥያቄ አልፎ የዓለም ትልልቅ መድረኮች አጀንዳ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ለስኬታማነቱም ሀገራዊ ለውጡን ደግፈው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ከለውጡ በኋላ ሴቶች ወደ ትልልቅ የመንግስት ሀላፊነቶች እንዲጡ መደረጉ እንዳስደሰታት የገለጸችው ደሞ ወጣት ኤደን ማርቆስ ናት።

ሀገራዊ ለውጡ ለሴቶች ተጠቃሚነት ቅድሚያ መስጠቱን ጠቁማ ለዚህም ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች።

ሌላኛው ወጣት ሀይደር ሁሴን በኢትዮጵያ ታረክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁልፍ የመንግስት ሀላፊነት በመያዝ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ተደርጓል ብሏል።

ይህን ተቀራርቦ የመስራት ባህል ለማስቀጠል ሀገራዊ ለውጡን ደግፎ እንደሚቀጥል ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም