የሀገራዊ ለውጡ አዲስ ምዕራፍ - የሌማት ትሩፋት - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ለውጡ አዲስ ምዕራፍ - የሌማት ትሩፋት
ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ ከመጋቢት 24/2010 በኋላ ትኩረት ከተሰጣቸውና ተተግብረው ስኬታማ ከሆኑት የልማት ኢኒሼቲቮች መካከል አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው። የሌማት ትሩፋት በዋናነት የከተማና የገጠር አርሶ አደሮችን በማቀናጀት፣ በአነስተኛ ቦታ ላይ ሁሉ የጓሮ አትክልትና የዶሮ እርባታን በማስፋፋት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ፕሮግራም ነው።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን ማለትም ወተት፣ ሥጋ፣ አሳ፣ እንቁላልና ማርን እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬን በስፋት በማምረት የሥርዓተ-ምግብ ማሻሻልን ዓላማ በማድረግ እየተተገበረ ያለ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሌማት ትሩፋትን በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት በምግብ ራስን አለመቻል የሀገርን ክብር ይነካል፣ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ካልቻለች ሙሉ ነፃነት ሊኖራት አይችልም ማለታቸው ይታወሳል።
በስንዴ ምርት የታየው ስኬት ወደ እንስሳት ሀብት ልማት (ወተት፣ እንቁላል፣ ስጋና ማር) መደገም እንዳለበትም አሳስበው ጤናማና አምራች ትውልድ ለመፍጠር ሌማታችንን በተመጣጠነ ምግብ መሙላት አለብን በማለት ማስገንዘባቸውም እንዲሁ።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በቂ እና አመርቂ ምግብ ማግኘት መሆኑን በመጠቆም በቂ የመጠን፣ አመርቂ ደግሞ የይዘት ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የሌማት ትሩፋት ግብ በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ በማድረግ የህፃናት መቀንጨርን መቀነስ፣ ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ፍጆታ የተረፈውን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሳደግና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ማሻሻል መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ይህ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ የተለያዩ የትኩረት መስኮች አሉት።
የላሞችን ዝርያ ማሻሻልና የወተት ምርትን ማሳደግ፣ የእንቁላልና የዶሮ ሥጋ ምርትን በየቤተሰቡ ተደራሽ ማድረግ፣ ዘመናዊ ቀፎዎችን በመጠቀም የማር ምርትን በጥራትና በብዛት መጨመር እንዲሁም ጥራት ያለው የስጋ ምርት ማቅረብ ቁልፍ ምሰሶዎች ናቸው።
ግብርናና የእንስሳት እርባታን የከተማ ግብርና አካል የማድረግ ሰፊ ንቅናቄ መፈጠሩ ከታዩ ለውጦች መካከል የሚጠቀስ ነው። የዶሮና የእንቁላል ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በብዙ ክልሎች የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችና የምርት መሰብሰቢያ እና ማከማቻ ማዕከላት ተስፋፍተዋል።
የሌማት ትሩፋት ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የገቢ ምንጭ ሆኗል። ከመደበኛው የሰብል ምርት በተጓዳኝ አርሶ አደሩ በየቀኑ ገቢ ማግኘት መቻሉ የኑሮ ደረጃው እንዲሻሻል በእጅጉ አግዟል።
በፕሮቲን የበለፀጉ ምግቦችን ለህጻናትና ለነፍሰ ጡር እናቶች ተደራሽ በማድረግ በኩል ለውጥ መታየቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአንድ ቀን ጫጩቶች፣ የተሻሻሉ የወተት ላሞችና ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ለአርሶ አደሩና ለከተማ ነዋሪው ተደራሽ መደረጋቸው፣ ቀደም ሲል በግዢ ብቻ ይሟሉ የነበሩ የእንቁላል፣ የወተትና የማር ምርቶች አሁን ላይ በብዙ ቤተሰቦች ጓሮ እንዲመረቱ አድርጓል።
ይህ ተሞክሮ በቤተሰብ ደረጃ የፕሮቲን አቅርቦትን በማሳደግ በሕፃናት ላይ የሚታየውን የምግብ እጥረትና መቀጨጭ ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን በተለይም የከተማ ግብርናን በማስፋት ነዋሪው በውስን ቦታ ምርታማ መሆን እንደሚችል በተግባር የታየበት እንደመሆኑ በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ታይተዋል።
በተጨማሪም፣ ጥራት ያለው የማርና የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተጀመሩ ጥረቶች የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ አዲስ በር ከፍተዋል።
የሌማት ትሩፋት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻልና የዜጎቿን የአመጋገብ ሥርዓት ለማሻሻል የጀመረችው ስትራቴጂካዊ ጉዞ አካል ሲሆን፣ ከመነሻው አንስቶ በምርት ዕድገት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በሥራ ባህል ለውጥ ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አሳይቷል።
ይህ ንቅናቄ በተለይ የእንስሳት ተዋጽኦን በየጓሮውና በየቤቱ ተደራሽ በማድረግ በሕፃናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨር እና የመቀጨጭ ችግር ለመቅረፍና አነስተኛ አምራቾችን የዕለት ገቢ ባለቤት ማድረግ አስችሏል።
የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሥነ ምግብ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል አርሶ እና አርብቶ አደሩም ይሁን የከተማ ነዋሪው በአካባቢው ያሉ አቅሞችን ሁሉ ወደ ልማት በመቀየር ሌማቱን ከመሙላት ባሻገር ለሌሎች ለመትረፍ የሚተጉበት ሀገራዊ ለውጡ ያስገኘወ ስኬታማ የንቅናቄ ፕሮግራም ነው፡፡
በአጠቃላይ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለዘላቂ ብልጽግና መሠረት የሚጥል ታላቅ ብሔራዊ ፕሮግራመ መሆኑን በተጨባጭ እያረጋገጠ ነው።