የሀገራዊ ለውጡ ትሩፋት የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ስርነቀል ለውጥ እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ለውጡ ትሩፋት የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ስርነቀል ለውጥ እያመጣ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ የሀገራዊ ለውጡ ትሩፋት የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ስርነቀል ለውጥ እያመጣ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በመዲናዋ አምስተኛው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ስራ ማስጀመርያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
የዚሁ አካል የሆነውና የተገልጋዩን እንግልት በመቀነስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት የሚሰጠው ማዕከል ለአገልግሎት በመብቃቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሀገራዊ ለውጡ የመንግሥትን አሠራር ስርነቀል በሆነ መልኩ ለቀየረው መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ስኬትና ሌሎቹም ውጤታማ ተግባራት ዋነኛው ምንጭ ነው ብለዋል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የሀገራዊ ለውጡ ትሩፋት መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
ማዕከሉ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ አቀናጅቶ ጊዜን፣ ወጪን፣ ጉልበትን በመቆጠብ እና እንግልትን በማስቀረት ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተለይ ተመጋጋቢ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አብዛኛው ነዋሪ በንግድ ስራ ላይ የተሰማራ መሆኑን አስታውሰው፤ የሚያጋጥማቸወን እንግልት በማስቀረት ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል ነው ያሉት።
አገልግሎቱ በብቁ የሰው ሀይል የተደራጀና ዘመኑን በሚመጥን አስተሳሰብና በላቀ የስራ ተነሳሽነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ለማገልገል መገንባቱን ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እና የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ በርካታ ስብሰባዎችን ለመታደም የሚመጡ አካላትና ቱሪስቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ በሚያስችል ሁኔታ መሰራቱንም ጠቁመዋል።