ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባራት ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ለገጠር ትራንስፎርሜሽን መሠረት የሚሆኑና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባራትን ማከናወኗን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የግብርና ምርታማነት ለምግብ ሉዓላዊነትና ለሀገራዊ ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ በለውጡ ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ እውን ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ፣ የግብርናው ዘርፍ ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ሆኖ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ስኬት እያስገኘ ነው፡፡
የበጋ ስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት፣ ኩታ ገጠም፣ የግብርና መካናይዜሽን እንዲሁም ሌሎችም ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘመናት ዘርፉ ሳይጠቀምበት የቆየውን ዕድል ለማስተካከል ከለውጡ ወዲህ በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም ስንዴን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ሀገሪቱ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት በመሰራቱ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
የዘርፉን ዋነኛ ተግዳሮት ለመፍታት ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ለማምረት እንዲሁም የግብርናውን ባህሪ የተረዳ የባንክ የብድር አቅርቦት ሥርዓት ለመዘርጋት መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛልም ነው ያሉት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የሚተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምርታማነት መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል ።
በአሁኑ ወቅት የአረንጓዴ አሻራ ተግባር በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ባህል እየዳበረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ የግብርና ምርምር ስራ ለዘርፉ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን ማምረት እንደሚቻል በምርምር ማረጋገጡን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
ከለውጡ በፊት በሄክታር 20 ኩንታል የነበረው የስንዴ ምርታማነት በአሁኑ ወቅት ወደ 36 ኩንታል ማደጉን ፕሮፌሰር ንጉሴ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በቆሎ በሄክታር ከነበረበት 20 ኩንታል ወደ 45 ኩንታል ከፍ ማለቱንና በቡና ምርታማነትም ትልቅ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት የጤፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ምርምር እየተከናወነ እንደሚገኝና የምርምር ሥራውም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ሜካናይዜሽን ለምርታማነት ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት አርሶ አደሩ በቀላሉ ሊጠቀማቸው የሚችላቸው የሜካናይዜሽን ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
የቀድሞው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በውስን የሰብል ዓይነቶች ላይ ብቻ ያተኮረና የሀገሪቱን እውነተኛ የምርታማነት አቅም ያላገናዘበ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር የፖሊሲ ጥናትና ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ መንግሥቴ (ዶ/ር) ናቸው።
ፖሊሲው በቂ የሕግ ማዕቀፍና አሠራር ያልነበረው ከመሆኑም በላይ የግሉ ዘርፍ በሂደቱ ላይ ተሳታፊ እንዳይሆን አድርጎ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ግብርና መር በሚል ይታወቅ የነበረው ይህ የቀድሞ መመሪያ በዘርፉ ላይ የነበሩ የአሠራር ክፍተቶች እንዲሰፉ ማድረጉንም በዝርዝር አመልክተዋል።
በአንጻሩ ከለወጡ ወዲህ ተግባራዊ የተደረገው የብዝሃ ኢኮኖሚ ስርዓት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ መሰረት ጥሏል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የዲጂታል ግብርና ዳይሬክተር ግሩም ከተማ (ዶ/ር)፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን መሠረታዊ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል አርሶ አደሩ ዘመናዊ አሰራርን እንዲከተል የሚያስችል ግልጽ አቅጣጫ ባለመኖሩ ውስንነቶች እንደነበሩ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን በዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ግልጽ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል።
በቀጣይ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ የኃይልና የኢንተርኔት ተደራሽነትን ሙሉ በሙሉ በማዳረስ ሁሉንም አርሶ አደር የዲጂታል ግብርና ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።