ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር  - ከጉስቁልና የኑሮ ዘዬ ወደ ሰብዓዊ ክብር ያሻገረ

በምህረት አንዱዓለም

የገጠር ኮሪደር ማለት የእያንዳንዱን አርሶ አደር ቤት እና የአኗኗር ዘዬ መቀየር ነው። ዓላማውም በቤተሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን ሕይወት በመቀየር እንደ ሀገር የምናስበውን ብልፅግና ማረጋገጥ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ሁሉም ነገር በፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ እንዲገባ መነሻው መጋቢት 24 ቀን ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ በጊዜ የለኝም መንፈስ የሚሮጡ ልጆቿን ይዛ በሚታይና በሚዳሰስ የለውጥ ትሩፋቶች ውስጥ እንድትገባም መሰረት የተጣለበት ዕለት ነው። በሁሉም ዘርፍ ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል። እየተመዘገቡ ከሚገኙት ለውጦች መካከል የገጠር ኮሪደር አንዱ ነው።


 

በአዲስ አበባ የተለኮሰው ከተማን ውብ፣ ጽዱ የማድረግ ርዕይ በክልል ከተሞችም እየተቀጣጠለ ይገኛል። ትናንት የታየ ከተማ ዛሬ በአዲስ ገጽታ እና ዘመናዊነት ነዋሪዎቹን አስደምሟል።

ይህ የለውጥ መንፈስ ለብዙ ዘመናት ተረስቶ የቆየውን ገጠሩንም እየዳሰሰው ነው። ለውጥ በገጠሪቱ ኢትዮጵያም እየተስፋፋ ይገኛል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመሠረተ ልማት ግንባታና በከተማ ዘመናዊነት የተመዘገበው ስኬት፣ አሁን አቅጣጫውን ወደ ገጠሩ የሀገሪቱ ክፍልም አዙሯል። በገጠር ድንቅ ዕይታን ፈጥሯል፤ የሕይወት መታደስንም አምጥቷል።

ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ2017 ዓ.ም በይፋ ያስጀመሩት የገጠር ኮሪደር ልማት፣ ዘመናዊነትን፣ ተስፋንና የተሻለ ሕይወትን ወደ አርሶ አደሩ ደጅ ያወረደ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ መጀመሩ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው።  

ይህ ኢኒሼቲቭ አርሶ አደሩን ከዘመናት የኋላ ቀርነት ቀንበር አላቆ ወደ ዘመናዊና ሰብዓዊ ክብር ወዳለው የአኗኗር ዘይቤ የሚያሸጋግር ብርቱ ድልድይ ሆኗል።

የገጠር ኮሪደር ልማት ለኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ ቤት ከመገንባት በላይ ትርጉም አለው። ይህ ልማት ገና ከጅምሩ አርሶ አደሩን ከምርት ትርፋማነት ባለፈ፣ ዘመናዊ የኑሮ ሥልትን እንዲላበስ እያደረገ ነው።


 

እያንዳንዱ አርሶ አደር በቤተሰብ ደረጃ ሕይወቱ ሲለወጥ ሀገራዊ ብልፅግና ትርጉም ይኖረዋል።

ዛሬ በኢትዮጵያ ገጠር የሚሰማው የምስራች ነው፤ የሚታየውም አዲስ ዓለም ነው። በገጠር ኮሪደር ወደ አዲስ ሕይወት የሚያሻግር የአኗኗር ዘይቤ የጀመሩ አርሶ አደሮች ትናንት ከከብቶች ጋር በአንድ ጣሪያ ስር ይኖሩ የነበረበት ሁኔታ ተቀይሯል።

ዛሬ ከአካባቢው ከተገኘ ድንጋይና አፈር ወደ ተገነባ ዘመናዊ ሞዴል ቤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገብተዋል። "ሰው ይኖርበት ከማይመስል ጎስቋላ ኑሮና ጣሪያ ወጥተናል፤  አሁን ብርሃን አይተናል" የሚሉትም ለዚሁ ነው።

የገጠር ኮሪደር ልማት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ቀደም ሲል እናቶች ለምግብ ማብሰያ እንጨት ፍለጋ የሚንከራተቱበት ዘመን አክትሟል። ዛሬ በባዮ ጋዝ ያበስላሉ። በእያንዳንዱ ጓሮ የሌማት ትሩፋት ፍሬ አፍርቷል። አርሶ አደሮቹ ዛሬ ማብሰያ ክፍላቸው (ኩሽና) የጸዳ፣ መኝታቸው ደግሞ ለሰው ልጅ ክብር የሚመጥን ሆኗል።

ይህ የገጠር ኮሪደር ልማት በአንድ አካባቢ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ለአብነት ብናነሳ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ሁልባረግ ወረዳ፣ እስከ ደቡብ ምዕራብ ጉራ ፈርዳ፣ ከጎንደሯ ሳይና ሰቢያ ቀበሌ እስከ የሀረር ሶፊ ወረዳ፣ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ መደ ጃለላ ቀበሌ እስከ ሲዳማ ዳራ ድረስ ዘልቋል። እነዚህን ለአብነት ጠቀስን እንጂ በሁሉም አካባቢ እየተስፋፋ ኢትዮጵያን በልማት ሰንሰለት እያስተሳሰረ ይገኛል።

ክልሎች ባላቸው ተፈጥሯዊ ፀጋና የራሱን አካባቢያዊ ግብዓት በመጠቀም፣ የራሱን የገጠር ሞዴል መንደር ዲዛይን እያደረገ፣ እየገነባ ስልጡን ኑሮን እየፈጠረ ይገኛል። ይህም አርሶ አደሩ በገዛ አቅሙና በአካባቢው ሀብት ቤቱንና ጓሮውን ማዘመን እንደሚችል ትልቅ ሠርቶ ማሳያ ሆኗል።


 

የኢትዮጵያ ገጠር ትናንት

ትናንት የኢትዮጵያ ገጠር በጭስ የታፈነ፣ እናቶች ለምግብ ማብሰያ እንጨት ፍለጋ የሚንከራተቱበት፣ ሰውና እንስሳት በአንድ ቤት የሚተኙበትና በሽታ የሚፈራረቅበት ነበር። አርሶ አደሩ ቢያመርትም ኑሮውን ማሸነፍ ያልቻለበት፣ የመለወጥ እሳቤ የተዳፈነበት የኋላቀርነት ዘመን ነበር። ከሁሉ በላይ የአንችልም መንፈስ አርሶ አደሩን ለዘመናት ተብትቦ ያቆየው መሆኑ የትናንት ገጠርን ያስታውሳል።

የኢትዮጵያ ገጠር ዛሬ

ዛሬ የኢትዮጵያ ገጠር እየተነቃቃ ነው። አርሶ አደሮች መለወጥ፣ ማሳካት፣ ሕይወታቸውን ማሻሻል እንደሚችሉ በተጨባጭ አይተዋል። የራሳቸውን ዘመናዊ ቤት በራሳቸው ዲዛይን መስራት ጀምረዋል። እናቶች በማገዶ ጭስ ዓይናቸው አይታመምም ምክንያቱም በባዮ ጋዝ ያበስላሉና። በሶላር ብርሃን ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ጓሯቸው በአትክልትና ፍራፍሬ ለምልሟል። ዛሬ ጀግንነት አቧራን ማራገፍ፣ ከቤት የተሻገረ ጥቅል ሕይወትን ማደስ ሆኗል።


 

የኮሪደር ልማት ወደ ገጠር ወርዶ አርሶ አደሩ በገዛ ቀዬው ኩሩ ዜጋ እንዲሆን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። የገጠር ኮሪደር ለአርሶ አደሩ ጤናማ፣ ዘመናዊና ከዓለም ጋር የተገናኘ ኑሮን የሚሰጥ ነው። የገጠር ኮሪደር በአርሶ አደሩ ቤት ውስጥ የሚታይና የሚጨበጥ ለውጥ እያመጣ ነው። ይህ ታሪካዊ ሽግግር የትናንት ጉስቁልናን እያስወገደ የነገን ተስፋ እየገነባ ነው። ዛሬ የገጠር ኮሪደር በደረሰባቸው መንደሮች ኑሮ ዘምኗል።


 

የኢትዮጵያ ገጠር ነገ

የነገዋ ኢትዮጵያ ገጠር መዳረሻ ምቹና ተስማሚ የሆነ፣ በገጠርና በከተማ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ጠቦ የሚታይበት ይሆናል። ነገ አርሶ አደሩ በገዛ ቀዬው ሆኖ ኢንተርኔት፣ የኤሌክትሪክ ሃይልና ንጹህ ውሃ የሚያገኝበት፣ እያንዳንዱ አርሶ አደር ባለሀብት ሆኖ ምርቱን ለዓለም ገበያ የሚያቀርብበት፣ ከስደትና ከልመና ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማውረስ የሚችልበት ነው። ይህ የልማት ተነሳሽነት ኢትዮጵያ የተሟላ ብልጽግናን ማረጋገጧ አይቀሬ የመሆኑ ሕያው ምስክር ነው። ለዚህ ስኬት ከሁሉም በይቻላል እሳቤ ትጋት ይጠበቃል።

ብልፅግናን እናረጋግጥ ሲባል በቁጥር የሚታይ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ በከተማም በገጠርም የእያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት መንካት አለበት። የዜጎች ሕይወት ሲነካ ለውጡ የሚጨበጥና የሚታይ ይሆናል፤ ያኔ ሰዎች እየተነቃቁና እየተጋገዙ የማይቆም ጥራት ያለው ዕድገት ማረጋገጥ ይቻላል።  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም