መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ዘመናዊ አገልግሎትን መስጠት እያስቻለ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ዘመናዊ አገልግሎትን መስጠት እያስቻለ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እያስቻለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
በመዲናዋ አምስተኛው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ማስጀመርያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ውጤት ተመዝግቧል።
የዚሁ አካል የሆነና የተገልጋዩን እንግልት በመቀነስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት የሚሰጥ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ መሶብ የአንድ ማዕከል ለአገልግሎት ወደስራ በመግባቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ማዕከሉ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ አቀናጅቶ ጊዜን፣ ወጪንና ጉልበትን በመቆጠብ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወደስራ መግባቱ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እያስቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በንግድ ላይ የተሰማሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚበዙበት በመሆኑ በተለያየ ጊዜ የሚያጋጥማቸውን እንግልት በማስቀረት ፈጣን አገልግሎት በማግኘት ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ በበቁ ሰዎች የተደራጀና ዘመኑን በሚመጥን አስተሳሰብና በላቀ የስራ ተነሳሽነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ለማገልገል መገንባቱንም ገልጸዋል።