ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች በዲጂታል የታገዘ ምቹና ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች በዲጂታል የታገዘ ምቹና ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመንግስትና የግል አጋርነት የመዲናዋን ነዋሪዎች የትራንስፖርት ችግር በዘላቂነት መፍታተ የሚያስችሉ 100 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን ስራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

የኤሌክትሪክ አውቶቡሶቹ የጉዞ ቲኬት ክፍያን ጨምሮ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥርዓትን በማካተት ከአየር ብክለት የጸዱ፣ ፈጣን፣ ዘመናዊና በርካታ ሰዎችን በምቾት የሚያጓጉዙ ናቸው።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች የትራንስፖርት መጨናነቅን በማቃለል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

ከተገልጋዮች መካከል አቶ አየለ ክብረት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱት ዘመናዊ አውቶቡሶች በዲጂታል የታገዘ ምቹና ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ችግሩን መቀነስ አስችለዋል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱን በስማርት ካርድ አማካኝነት በማግኘታቸው ጊዜ እንደቆጠበላቸውና ከእንግልት እንደታደጋቸው ጠቁመዋል፡፡


 

ሌላው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ገብረጊዮርጊስ ሃይሌ በበኩላቸው፤ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠታቸው ባለፈ ጭስ አልባና ጽዱ በመሆናቸው በከተማ ፅዳትና ውበት ላይ የጎላ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡


 

የኤሌክትሪክ አውቶቡስ ካፖቴን ዳዊት ግርማ፤ ተሽከርካሪዎቹ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን በፍጥነትና በምቾች በማስተናገዳቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ ሆነዋል ብለዋል፡፡


 

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመዲናዋ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋና በተሻለ ፍጥነት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ካፒቴን አማኑኤል ቴዎድሮስ ናቸው፡፡


 

ካፒቴን ኤፍሬም ሀብታሙ በበኩላቸው፤ ተጠቃሚዎች የክፍያ ስርዓቱ በዲጂታል መንገድ እንዲፈጽሙ በማድረግ የአውቶቡሶችን ምልልስ በመጨመር አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

የግሪን አዲስ (ቬሎሲቲ) ትራንስፖርት ዋና ሥራ አስኪያጅ ግዛው ዓለሙ፤ ተሽከረካሪዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች በመጨመር ለህብረተሰቡ አስተማማኝ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም