ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ወደ አዲስ የምርታማነት ምዕራፍ አሸጋግሯል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውድቀትን በመግታት ወደ አዲስ የምርታማነት ምዕራፍ አሸጋግሯል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ተቀርፀው ወደ ተግባር የተቀየሩ የብዝሃ-ኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች ዛሬ ላይ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም የኢንዱስትሪ ምርታማነትን የሚያሳድግ መዋቅራዊ የድጋፍና ክትትል ሥርዓትን በመፍጠር በወጪ ንግድና በተኪ ምርት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እያረጋገጠ ይገኛል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በቅርቡ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ያረጋገጡት፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠረው አስቻይ ምኅዳር ውድቀትን በመግታት ወደ አዲስ የምርታማነት ምዕራፍ ያሸጋገር አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ነው።


 

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን የምርታማነት ምኅዳር በማስፋት ማርሽ ቀያሪ አቅም እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል።

የውጭ ምንዛሬ ክምችት አቅምን በማሻሻል አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የፋይናንስ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መሻሻል እንዲፈጠር ማድረጉንም አብራርተዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፍ የምርታማነት ማበረታቻ ምኅዳርን በማስፋት በተኪና ወጪ ንግድ ምርት ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ ምርታማነት የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተተገበሩ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕድገት አቅጣጫ እሳቤዎች ፍሬ እያፈሩ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የኢንዱስትሪ ዘርፍ የቦታ፣ የግብር እፎይታ፣ የፋይናንስ አቅርቦትና ተያያዥ ማነቆዎችን መፍትሔ በመስጠት የባለድርሻ ተቋማትን ቅንጅት ማጎልበት እንዳስቻለ ተናግረዋል።


 

በአምራች ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የሚደረገው ድጋፍም ዘርፉ ከነበረበት ዝቅተኛ የማምረት አቅም አጠቃቀም አሁን ላይ ከ66 በመቶ በላይ በማሸጋገር የሀገር ውስጥና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደጉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ እሳቤም 96 የምርት ዓይነቶችን በመተካት ዓለም አቀፍ የንግድ ሚዛንን ማስጠበቅ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን አንስተዋል።

በኢንዱስትሪዎች የተፈጠረው የተኪ ምርት አቅም ከሦስት ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ በማዳን የንግድ ሚዛንን የሚያስጠበቅ አመርቂ ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።

አዳዲስ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን በማስፋት፣ በስራ ዕድልና በወጪ ንግድ ምርታማነትም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት የአርሶ አደሮችን ምርታማነት በማሳደግ በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ሽግግር አወንታዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በዚህም በግብርና ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማጎልበት ከሀገር ውስጥ ፍጆታን ከማሟላት ባለፈ ለወጪ ንግድ አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።

በቀጣይም በሁሉም ክልሎች የግብርና ማቀነባበሪያ ማዕከላትን በመገንባት የግብርና ምርታማነትን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም