ኮሚሽኑ ያዘጋጀው መድረክ አጀንዳዎቻችንን በማቅረብ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው -የትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ያዘጋጀው መድረክ አጀንዳዎቻችንን በማቅረብ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው -የትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት
አዲስ አበባ፤መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር መድረክ አጀንዳዎችን በማቅረብ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ተሳታፊዎች ገለጹ።
ከትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ የመጀመሪያው ዙር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ኢንጅነር ታፈረ ህሉፍ ኮሚሽኑ የጀመረው የምክክር ሂደት የሚደነቅ መሆኑን በመጥቀስ፥ ዛሬ የተጀመረው መድረክም አሳታፊና አስደሳች ነው ብለዋል።
ልዩነት ተፈጥሯዊ መሆኑን ገልጸው፤ መድረኩ የተለያዩ አጀንዳዎችን በማቅረብ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው የአጀንዳ ማሰባሰቡ ተሳታፊ አንተነህ ምትኩ በበኩላቸው መድረኩ በብዙዎች ዘንድ ሲጠበቅ የቆየ ቢሆንም ዛሬ በተግባር መጀመሩን አድንቀዋል።
አለመግባባቶችን በምክክር ከመፍታት የተሻለ ነገር እንደሌለ በማንሳት፥ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ጠቀሜታው የላቀ ነው ያሉት አቶ አንተነህ፥ የምክክርና የውይይት ባህልን ለማጎልበት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
መድረኩን በጉጉት ስንጠባበቀው ነበር ያሉት አብዱ አብዱልቃድር እና ሰርካለም ወርቅነህ (ዶ/ር)፥ አጀንዳዎችን በማቅረብ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን አስረድተዋል።
ወደ ፊት የተሻለ ትውልድ ለመፍጠርና ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ ምክክር ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።