ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ በአዲስ አበባ መጀመሩ ትክክለኛ ውሳኔ ነው - ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም

አዲስ ኣበባ፤ መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ በአዲስ አበባ መጀመሩ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ሲሉ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ገለፁ።

ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ቀደም ሲል የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ በመሆን ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብና ተሣታፊዎችን የመለየት ስራ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጋቢት 25/2018 ዓ.ም የሚካሄደው የምክክር መድረክ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ከትግራይ እና ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ታዳሚያን እየተሳተፉበት ነው።

ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ለኢዜአ እንደገለጹት ዋናው የሀገራዊ ምክክር መድረክ ዓላማ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ዓይነት ጥያቄዎች እና ችግሮች በጦርነትና በጉልበት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት አለባቸው የሚል ነው።

ከሚሽኑ የውይይት መድረኩን በትግራይ ክልል ለማካሄድ በተለያዩ ጊዜያት ብርቱ ጥረት ቢያደርግም በክልሉ ያለው በሀይል ብቻ የሚተማመነውና ለሰላማዊ ውይይቱ ፈቃደኛ ያልሆነው ህገ-ወጥ ቡድን አማካኝነት ለማካሄድ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ትግራይ ከሌሎች ክልሎች የተለየች አይደለችም ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፤ በትግራይ ክልል ምቹ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ የውይይት መድረክና አጀንዳ የማሰባሰብ ስራው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መደረጉ ትክክለኛና አግባብነት ያለው ውሳኔ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዋናውን የኮሚሽኑን ተልዕኮ ለማሳካት ወደ ውይይት መድረክ መምጣትና ችግሮችን በመመካከር መፍታት አዋጭነት ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።

በሰላም እና በውይይት የሚያምን የትግራይ ማህበረሰብ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ባለው የምክከር መድረክና አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ላይ በቀናነት እየተሳተፈ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች የተለያዩ ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስታውሰው የትግራይ ክልል ጥያቄዎች በመመካከርና በመወያየት እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚፈቱ እንደሆኑ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም