ቀጥታ፡

ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን የመቆጣጠርና ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል  

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦ ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን የመቆጣጠርና ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። 

ቋሚ ኮሚቴው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የ2018 በጀት ዓመት የ8 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።  

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ በነዳጅ አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነትና በአጭር ጊዜ ለመፍታት ግብ ተቀምጦ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትና በዓለም አቀፍ ቀውስ ምክንያት ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በሀገርና በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳያሳድርና በፍትሐዊነት ለመምራት መንግሥት የቅድሚያ አሰጣጥ ውሳኔ አሳልፎ እየሰራ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ 

በሌላ መልኩም ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ጨምሮ በተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ 

በነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ዙሪያ ሕገ-ወጥ ድርጊት የፈጸሙ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

የነዳጅ ሥርጭቱን ፍትሐዊና የተሳለጠ ለማድረግ በሚኒስቴሩ የሚመራና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ልዩ የሁኔታዎች መከታተያ ክፍል መቋቋሙንና በግብረ ኃይል የታገዘ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ልዩ የመከታተያ ክፍሉ በማዕከል የሚመራ ሲሆን የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና አጠቃቀምን የሚከታተል፣  ውሳኔዎችን የሚያቀርብና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የሚለይ መሆኑን ገልጸዋል። 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አይሻ ያህያ በበኩላቸው፤ በነዳጅ ግብይት፣ ሥርጭትና ቁጥጥር ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

ሆኖም በቀጣይ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የሚሰማሩ አካላትን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡  

የነዳጅ ማደያዎች በአግባቡ አገልግሎት እየሰጡ ስለመሆኑ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ሰብሳቢዋ፥ የነዳጅ ተደራሽነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም