በለውጡ ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ በዘርፉ መነቃቃትን በመፍጠር መዋቅራዊ ሽግግሩን እያፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በለውጡ ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ በዘርፉ መነቃቃትን በመፍጠር መዋቅራዊ ሽግግሩን እያፋጠነ ነው
ሐዋሳ፤ መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ በዘርፉ መነቃቃትን በመፍጠር መዋቅራዊ ሽግግሩን እያፋጠነ መሆኑን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ፡፡
መጋቢት 24/2010 የተደረገውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻዎችና ፕሮግራሞች ለዘላቂ ልማትና እድገቱ ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ በዘርፉ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን መዋቅራዊ ሽግግሩን እያፋጠነ ይገኛል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ገብረክርስቶስ ኑርዬ(ዶ/ር) እንደተናገሩት በለውጡ መንግስት የኢኮኖሚ እሳቤን ከግብርና መር ወደ ብዝሃ ዘርፍ ለመቀየር በተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው፡፡
በተለይም አምስቱ የኢኮኖሚ መሰረቶችን በማስተሳሰር የተከናወኑ ተግባራት ሁሉን አቀፍ ልማት ማስመዝገብ የሚያስችል አቅምን ፈጥረዋል ብለዋል፡፡
በበጋ መስኖ ልማት ዓመቱን ሙሉ የማምረት አቅም በማዳበር ምርታማነትን ማሳደግ እንደተቻለና የምርት አቅርቦትና ገበያውን ማረጋጋት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት የተጀመሩ የገበታ ለሀገርና ለትውልድ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጨምሮ በከተሞች የተጀመረው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማትም በኢኮኖሚው ዘርፍ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚ ዘርፉ የተቀረጹ አዳዲስ ፖሊሲዎች ያስገኙት ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው በአመራር ቁርጠኝት በመስራት ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪና የተማሪዎች ዲን ማርቆስ ማቲዎስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት 8 ዓመታት የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማነቃቃትና ግብርናውን ለማዘመን(ሜካናይዝድ) ለማድረግ የተቀረጹ ፖሊሲዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው፡፡
በተለይም በሃሀገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጡ መነሻ የተነደፉ የበጋ መስኖ ስንዴና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮች የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲፈጠር አድርገዋል ብለዋል፡፡
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የፈጠረው እድል ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት እየስቻለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢንስቲትዩቱ የማኑፋክቸሪንግ መካነ-ትምህርት ዲን ካሳሁን ጋሹ(ዶ/ር) ናቸው፡፡
በለውጡ ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉ ፖሊሲዎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከማስተማር ጎን ለጎን አምራች እንዲሆኑ ማድረጉን የጠቀሱት ዲኑ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን በማጠናከር እንደሀገር ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር የበኩላችንን እያበረከትን እንገኛለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ጨምሮ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተፈጠሩ ምቹ እድሎች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አበርክቶውን የሚያሳድግ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡