ቀጥታ፡

በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሰረት የጣሉ ናቸው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሰረት የጣሉ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ገለጹ።

"ቃል በተግባር ፣ ከምርጫ እስከ ምርጫ" በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አዘጋጅነት የክልል መንግስት ቢሮዎች እና ተቋማት የተሳተፉበት ኤግዚቢሽን በኦሮሞ ባህል ማዕከል ተከፍቷል።


 

የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ባለፉት የለውጥ ዓመታት የክልሉን ህዝብ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።

የለውጥ ዓመታቱ በክልሉ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄ ያገኙበት እና ትክክለኛ የብልጽግና ጉዞ የተጀመረበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስትም በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራቱ ከተስፋ ወደ ተጨበጠ ብርሃን ሽግግር ለማድረግ እያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል።

ከኢኮኖሚ ልማት አንጻርም በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትልቅ ውጤት መምጣቱን ጠቅሰው፤በኢንዱስትሪ፣በማዕድንና በቱሪዝም ዘርፎች የተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የክልሉ መንግስት ተነጥለው የሚንቀሳቀሱ አካላት የሰላምን አማራጭ እንዲከተሉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ውጤት መምጣቱን አብራርተዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሰረት የጣሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያዘጋጀው ኤግዚቢሽንም ባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በበኩላቸው፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የክልሉ መንግሥት የገባውን ቃል በተግባር እየፈጸመ መሆኑን አንስተዋል።

የክልሉ መንግስት በአንድ በኩል የህግ የበላይነትን እያስከበረ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የልማት ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ማከናወን የቻለበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኤግዚቢሽኑ ህዝቡ በመንግስት ስራዎች ላይ ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖረውና የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በኤግዚቢሽኑ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ የተገኙት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ፤ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ሀገሪቱን ከጥገኝነት ወደ አምራችነት የቀየሩ ታሪካዊ ስራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንም የመንግስትን ፖሊሲዎች፣ስልቶችና የልማት ውጤቶች ለህዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም