ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ 7ኛውን ዓለም አቀፍ የክፍያ ሚዛንና የ2025 የብሔራዊ ሂሳቦች ሥርዓት ለመተግበር እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ስርዓቷን ለማዘመን 7ኛውን ዓለም አቀፍ የክፍያ ሚዛንና የ2025 የብሔራዊ ሂሳቦች ሥርዓት ለመተግበር እየሠራች  እንደምትገኝ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሀፅዮን ገለጹ። 

የብሔራዊ ሂሳቦች ሥርዓት 2025- (System of National Accounts 2025) የአንድን ሀገር አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወይም የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትን (GDP) ለመለካት የሚያገለግል ዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ መመሪያ ነው።


 

የብሔራዊ ሂሳቦች ሥርዓት 2025- 7ኛው የክፍያ ሚዛን ማኑዋል- BPM7 (Balance of Payments Manual 7th Edition) በአንድ ሀገር እና በሌላው ዓለም መካከል ያለውን የገንዘብና የንግድ ልውውጥ (የክፍያ ሚዛን) ለመመዝገብ የሚያገለግል መመሪያ ነው። 

የአፍሪካ ህብረት ስታትስቲክስ ኢንስቲትዩት እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት በክፍያ ሚዛን (BPM7) እና በ2025 የብሔራዊ ሂሳቦች ሥርዓት (SNA 2025) ላይ ያተኮረ መድረክ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሐ-ፅዮን በዚሁ ወቅት አፍሪካ እ.ኤ.አ የ2008 የብሔራዊ ሂሳብ አያያዝ ስርዓትን (SNA 2008) እና የክፍያ ሚዛን ማኑዋል (BPM6) በመተግበር ረገድ የሚደነቅ እድገት አስመዝግባለች ብለዋል። 

ይሁን እንጂ  ከዓለም ተለዋወጭ ሁኔታ አንጻር የኢኮኖሚ ሽግግርንና መዋቅርን ሙሉ በሙሉ ለመረዳትና ለመለካት አሁንም ከፍተኛ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

እንደ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ኢ-መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶች እና መሰል ጉዳዮች በቀደሙት አሠራሮች ለመለካት አስችጋሪ መሆኑንም በአብነት ጠቅሰዋል።

አዲሶቹ የብሔራዊ ሂሳቦች ሥርዓት 2025ና  7ኛው የክፍያ ሚዛን ማኑዋል የስታትስቲክስ ማዕቀፎችን ለማሻሻል ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የስታትስቲክስ ስርዓትን ለማዘመን ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስታትስቲክስ ሥርዓቶቹን ወደ ተግባር ለማስገባት አስቀድማ ዝግጅት መጀመሯንም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርትን ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አንጻር መልሶ የማደራጀትና የማጣጣም ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መሪነት የክፍያ ሚዛን ስታትስቲክስን የማሻሻልና የመንግሥት ፋይናንስ መረጃዎችን ጥራት የማሳደግ ተግባራት በትኩረት እየተተገበሩ መሆኑን አብራርተዋል።

ዘመናዊ የስታትስቲክስ ሥርዓት መዘርጋቱ የአጀንዳ 2063 እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እንዲሁም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እምነትን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የአፍሪካ ህብረት ስታትስቲክስ ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ ስታትስቲክስ ዳይሬክተር አዱም ጋጎሉም በበኩላቸው፣ በአህጉሪቱ የስታትስቲክስ ሥርዓቶችን ለማጠናከርና ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ከአፍሪካ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የ2025 የብሔራዊ ሂሳቦች ሥርዓት (SNA)  እና የክፍያ ሚዛን (BPM7) በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በቀጣናዊ ትስስርና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የተሻለ የፖሊሲ ቀረጻ እንዲኖር ያስችላሉ ነው ያሉት።


 

በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የስታትስቲክስ መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር ጂም ቴብሬክ፤ በአፍሪካ የስታትስቲክስ ዘርፍን ለማዘመን ዓለም አቀፍ ሥርዓቶችን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የአፍሪካ ህብረት ስታትስቲክስ ኢንስቲትዩት ስለ ሀገራት ኢኮኖሚና ዓለም አቀፋዊ ትስስር አስተማማኝ መረጃ በመስጠት ረገድ  ሚናውን  መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም