በኢትዮጵያ የለውጡ ዓመታት ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር፣ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ተሳትፎ የታየበት ነው- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የለውጡ ዓመታት ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር፣ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ተሳትፎ የታየበት ነው- ምሁራን
ሆሳዕና ፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ) ፡-በኢትዮጵያ የለውጡ ዓመታት ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር፣ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።
በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ባለፉት ስምንት ዓመታት በሁሉም መስኮች እመርታዊ ውጤት መምጣቱ የሚታወቅ ነው።
በግብርና ልማት አዳዲስ ኢኒሸቲቮችን ጨምሮ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከራስ ተርፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተቻለበት ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጥሯል።
በቱሪዝም፣ ማእድን፣ የኢንዱስትሪ ልማትና በዲጅታል ቴክኖሎጂም ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን መናገር ይቻላል።
የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎች ስኬቶችን በተግባር ያረጋገጠበት ስለመሆኑም በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።
በተለይም በጠላትነት፣ በመገፋፋትና አግላይነት የሚታወቀውን የፖለቲካ ምህዳር አሳታፊ፣ አካታችና ሰፊ ምህዳር የተፈጠረበት ማድረግ መቻሉን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙላለም ኃይለማርያም፤ ለውጡ ሲመጣ በውጭና በሀገር ውስጥ በጠላትነትና አሸባሪነት ጭምር የተፈረጁ ፖለቲከኞችን ለሰላማዊ ትግል ያሰባሰበ መሆኑ ትልቅ ውሳኔ እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በውጭም በውስጥም የነበሩ ፖለቲከኞች በተፈጠረላቸው ምቹ ምህዳር ፓርቲ መስርተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማድርግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በምርጫ የመንግስት ስልጣን የያዘው ገዥ ፓርቲ ለተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ተቋማትን የመምራት እድል በመስጠት ጭምር አሳታፊና አካታችነቱን በተግባር ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
በዩኒቨርሲቲው በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል የሰላምና ግጭት ጥናት መምህር ጌታሁን አበራ፤ የለውጡ መንግሥት ባለፉት ስምንት ዓመታት በሁሉም መስኮች የሚታዩ እና የሚጨበጡ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
በተለይም በፖለቲካው መስክ የቆዩ ስብራቶችን በመጠገን ሀገራዊ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጽናት ረገድ አበረታች ውጤቶች መጥተዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የመጠላለፍና የጥላቻ ፖለቲካ አብቅቶ በሀገሩ ጉዳይ ሁሉም ተሳትፎና አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እድል የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።
የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የመንግስት ተቋማትን በሃላፊነት መምራታቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የለውጡ ዓመታት ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር፣ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ታሳትፎ የታየበት መሆኑን ምሁራኑ ተናግረዋል።