ቀጥታ፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኩታ ገጠም የሚታረስ መሬት 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኩታ ገጠም የሚታረስ መሬት 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የግብርና ምርታማነት ለምግብ ሉዓላዊነትና ለሀገራዊ ክብር" በሚል መሪ ሐሳብ በለውጡ ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ እውን ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ፣የግብርናው ዘርፍ ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ሆኖ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ረገድ ስኬት እያስገኘ ነው፡፡

እንደ የበጋ ስንዴ ምርት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ሌማት ትሩፋት፣ ኩታ ገጠም፣ የግብርና መካናይዜሽን እንዲሁም ሌሎችም ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ መንግስት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በዘርፉ ባለ አነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን በበቂ ሁኔታ አለመደገፍ፣ ገበያ ተኮር ያለመሆን እንዲሁም ዘመናዊ የግብርና ስርዓትን ባለመከተል የምርታማነት ማደግ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ በርካታ የፖሊሲ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ዘላቂነትን ታሳቢ ያደረገ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መቀረጹ፣ ከፍተኛ የማዳበሪያ ድጎማ መደረጉ፣ ከቀረጥ ነፃ የሜካናይዜሽን አቅርቦትና በዲጂታል የተደገፈ የግብርና አገልግሎት መስፋፋቱ፣የተፈጥሮ ሀብትን አውቆ መጠቀም መቻሉና የመሬት ሊዝ መብት መጠናከሩ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኩታ ገጠም የሚታረስ መሬት 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን ገልጸው፥ ይህም ከለውጡ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከ14 እጥፍ በላይ ማደጉን ጠቅሰዋል፡፡

በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ፣በተፈጥሮ ጥበቃና ደን መልሶ ማልማት 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዲያገግም መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የግብርና ምርታማነት መጠን ከ56 በመቶ በላይ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰው፥ የሰብል ምርት በሶስት እጥፍ ማደጉንም ጠቁመዋል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጀመሩን ጨምሮ በዘርፉ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዘርፉን በቴክኖሎጂ ይበልጥ ለመደገፍም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሠረት የግብርና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የማከናወን ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም