ቀጥታ፡

በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ይሰራል - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

የአሶሳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት ለዜጎች ወጪ ቆጣቢ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እያስቻለ ነው።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀላል እና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ መልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ አዎንታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም አንስተዋል።

የአሶሳ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በአጭር ጊዜ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉ በከተማዋ እየተከናወኑ ለሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች አጋዥ ከመሆን ባለፈ የዲጂታል አገልግሎትን ተደራሽ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አብዱልከሪም አብዱራሂም በበኩላቸው ማዕከሉ በከተማዋ የሚሰጡ ወሳኝ አገልግሎቶችን በማዘመን የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ ያግዛል ነው ያሉት። 

ማዕከሉ በአራት የክልል እና በሁለት የፌዴራል ተቋማት የተጀመረ ሲሆን 23 የተለያዩ አገልግሎችን እንደሚሰጡ ነው የተናገሩት።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም