ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድና ተጠቃሚ በማድረግ ያሳካቻቸው ውጤቶች ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን እያሳደጉ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድና ተጠቃሚ በማድረግ ያሳካቻቸው ውጤቶች ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን እያሳደጉ መሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ እያስተናገደች እንደምትገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከኡጋንዳ ቀጥሎ ሁለተኛ ሀገር ስትሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ስደተኞች የልማት አጋር ሆነው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥራለች።

በፈረንጆቹ 1951 የወጣውን ዓለም አቀፉን የስደተኞች ኮንቬንሽን በመተግበር ስደተኞችን በላቀ ደረጃ እየተንከባከበች መሆኑን ጠቁመው፥ ስደተኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ስደተኞች ትምህርት፣ጤና እና የምግብን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ በርካታ ተጨባጭ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፥ ስደተኞች ከተቀባይ ማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን የሚያጠናክሩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።

ስደተኞች ተጠልለው በሚገኙባቸው አካባቢዎች ካለው ተቀባይ ማህበረሰብ ጋር መስተጋብራቸውን በማጠናከር በልማት እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የስደተኞችን መብቶች በማክበር፣ ከዜጎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሏ እንዲሁም ስደተኞችን በመንከባከብ እና ተጠቃሚ በማድረግ ያሳካቻቸው ውጤቶች ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷ እንዲጎላ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉና ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ስደተኞች የኢትዮጵያ አምባሳደሮች በመሆን ስሟን በበጎ እያስጠሩ እንደሚገኙ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፥ ይህም ለቀጣናዊ ትስስር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም