ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከነበረው እጅጉን በተሻለ ለንግድ ዝግጁ ናት

አዲስ አበባ፤መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከነበረው እጅጉን በተሻለ ለንግድ ዝግጁ መሆኗን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት በInvest in Ethiopia 2026 ፎረም፤ ከቻይና፣ ፖላንድ፣ ህንድ ሲንጋፖር እና ኬንያ ከመጡ አጋሮች ጋር የ13.1 ቢሊዮን ዶላር ታሪካዊ የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈራረሙን አመልክቷል።

በታዳሽ ኃይል፣ በማዕድንና በአረንጓዴ አሞኒያ ዘርፎች ላይ ያተኮሩት እነዚህ ስምምነቶች የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳችን ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጉልህ ማሳያ መሆናቸውን ገልጿል።

የውጭ ምንዛሬ ተመን ሊበራላይዜሽን፣ እና የባንክና ቴሌኮም ዘርፎችን ለንግድ ማህበረሰቡ ክፍት ማድረግ የመሳሰሉ ቆራጥ እርምጃዎች ግልጽና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠራቸውን በተጨባጭ ማረጋገጡን ነው ነው ያስታወቀው።

ይህም በዘመናዊ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አማካኝነት ለዓለም አቀፍ ገበያ ምቹ መዳረሻን መፍጠሩ ተጠቅሷል።

‎ይህ ዕድገት በሁሉም ስትራቴጂካዊ ዘርፎች በግልጽ እየታየ እንደሚገኝ የገለጸው ጽህፈት ቤቱ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የተንተራሰው የሀገራችንን የታዳሽ ኃይል ሀብትን በመጠቀም በሶላር ምርት እና በሃይድሮጅን ፕሮጀክቶች ላይ የተገኘው እመርታ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የማዕድን ዘርፍ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራበት እንደሚገኝ አመልክቷል።

የኢንዱስትሪ ዕድገታችን አዲስ በሚገነቡት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እየተፋጠነ ሲሆን፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፉም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በልህቀት እየተመራ መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ትስስር እና በባህላዊ ቅርሶቻችን የታጀበችው ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ንግድና ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ መሆኗንም እንዲሁ።

ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ለላቀ አጋርነት እንጋብዛለን፤ ኢትዮጵያ ከነበረው እጅጉን በተሻለ ለንግድ ዝግጁ ናት ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም