ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት የአፋር ክልል ህዝብ እምቅ ሃብቶቹን በማልማት እመርታዊ ማንሰራራት ላይ ይገኛል

ሰመራ፣መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦በለውጡ ዓመታት የአፋር ህዝብ እምቅ ሃብቶቹን በማልማት በተለይም በግብርና፣በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና ሌሎችም መስኮች እመርታዊ ማንሰራራት ላይ እንደሚገኝ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ።

በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ የመደመር መንግስት ሀገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ፣በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መስኮች እመርታዎች እየተመዘገቡ ቀጥለዋል።

በተለይም ታዳጊ የሚል መለያ ተሰጥቷቸው በፖለቲካው መስክ "አጋር" እየተባሉ የነበሩ ከለውጡ በፊት የዳር ተመልካች ነበሩ።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ግን ሁሉም ክልሎች በሀገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ እኩል የሚሳተፉበትና የሚወስኑበት እድል ተፈጥሮላቸዋል።

በኢትዮጵያ አሳታፊ፣አካታችና ሁሉን አቀፍ የሆነ የማህበራዊ፣ ፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምህዳር የተፈጠረላቸው መሆኑን ባለፉት ሰባት ዓመታት በተግባር ማየት ተችሏል።

በዚህ አንፃር በለውጡ ዓመታት በአፋር ክልል የታየውን ሁለንተናዊ ልማትና የህዝቡን ተጠቃሚነት በተመለከተ ኢዜአ የአፋር ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ አቶ መሐመድ ዓሊ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ሃላፊውም በማብራሪያቸው፥ከለውጡ በፊት የአፋር ክልል ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ እንዳይወስን አጋር እየተባለ ተገፍቶ የኖረ መሆኑን አንስተዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ አሳታፊ፣ አሰባሳቢ እና የጋራ የሆነ ትርክት በመፈጠሩ የአፋር ክልል ህዝብ በሀገሩ ፖለቲካ ጉዳይ የዳር ተመልካች መሆኑ ቀርቶ እኩል ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ መሆን ችሏል ብለዋል።

የባለፈው ስርዓት ሲያራምደው በቆየው ፖለቲካ የአፋር ክልል ህዝብ አጋር እየተባለ በሀገሩ ጉዳይ የዳር ተመልካች ሆኖ መቆየቱ የሚያስቆጭ መሆኑን አንስተው፥ የመጣው ሀገራዊ ለውጥ ለክልሉ ህዝብ ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለውጡን ተከትሎ የአፋር ክልል ህዝብ በሀገሩ ፖለቲካ ጉዳይ የዳር ተመልካች መሆኑ ቀርቶ እኩል ተሳታፊና ውሳኔ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ህዝብ በለውጡ ዓመታት እምቅ ሃብቶችን በማልማት በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣በቱሪዝም እና ሌሎችም መስኮች እመርታዊ ማንሰራራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት በነፃነት ራሱን በራሱ በማስተዳደር ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ገና ብዙም ያልተነካ እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና የልማት አቅም ያለው በመሆኑ የልማት ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም