በባህር ዳር ከተማ 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ታአማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆና እንዲጠናቀቅ በትብብር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ታአማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆና እንዲጠናቀቅ በትብብር እየተሰራ ነው
ባህር ዳር፤ መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፡- በባህር ዳር ከተማ 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ታአማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆና እንዲጠናቀቅ በትብብር እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለፀ።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በባህር ዳር ምርጫ ክልል የሚሳተፋ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።
በባህር ዳር ምርጫ ክልል 11 ፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ከማስመዝገባቸው ባለፈ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች የምረጡኝ ቅስቀሳ እያካሄዱ ናቸው።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሞላ ሁሴን በውይይት በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ በከተማዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች በ7 ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፖሊሲዎቻቸውን ቀርጸው ለህዝብ እያስተዋወቁ ናቸው ።
ፓርቲዎቹ ምርጫው ተአማኒ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ ያሉት ሰብሳቢው ይህም ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፓርቲዎቹ በየጊዜው እየተገናኙ ምርጫውን ስኬታማ ለማድረግ በጋራ በመምከር የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ ያሉት አቶ ሞላ ከዚህ በተጓዳኝ በሰላምና በልማት ዙሪያ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፓርቲዎቹ ሀገረ መንግስቱን ለማፅናትና የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማስፋት በሚያስችሉ ተግባራት ላይም በቅንጅት አየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም መጪው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፋትሃዊ፣ የህዝብን ተሳትፎና አመኔታ ያረጋገጠ እንዲሆን በጋራ ምክር ቤቱ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ምርጫ የዴሞክራሲ ስርዓት ዋነኛ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም አባላቶቻቸውን በማስተማር ላይ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በምርጫ ሂደቱ ስኬቶች በጋራ በመስራትና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተነጋግሮ በመፍታት ለምርጫው የላቀ ውጤታማነት ሁሉም ፓርቲ አይተኬ ሚናውን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።