በለውጡ መንግስት እሳቤ የተቀየሰው በሀገር ጉዳይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በለውጡ መንግስት እሳቤ የተቀየሰው በሀገር ጉዳይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል
ጅማ፤መጋቢት 23/2018(ኢዜአ)፦በለውጡ መንግስት በመደመር እሳቤ የተቀየሰው በሀገር ጉዳይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የለውጡ መንግሥት የፖለቲካ ዕይታ ፓርቲዎች የተለያዩ አሰላለፎች እና መረዳቶች ቢኖሯቸውም ለጋራ ሀገር ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት በማድረግ በትብብር መሥራትን ሥልጣን እስከ ማጋራት የሚገለፅ ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ይኸው ዐቢይ እሳቤ በትብብርና በጋራ መሥራት እውን ሆኖ ወደ ተግባር መለወጡን መመልከት ተችሏል።
ይህንንም አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤በለውጡ መንግስት በመደመር እሳቤ የተቀየሰው በሀገር ጉዳይ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ምሁራኑ በማብራሪያቸው የለውጡ መንግስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብትና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ለማድረግ የጀመራቸውን ስራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ደረጄ ገላሳ መንግስት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሀገር ግንባታ ሂደት በጋራ መስራቱ ለሰለጠነ ፖለቲካ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።
ይህም ፓርቲዎቹ በፖለቲካ ርዕዮት ቢለያዩም በሀገር ጉዳይ ተቀራርበው የመስራት ባህል እንዲያዳብሩ የራሱ ድርሻ እንዳለው አክለዋል።
ተግባሩም ከዚህ ቀደም የነበረን አፍርሶ የመገንባት እሳቤን በማስቀረት በመደመር እሳቤ ሀገርን የማስቀጠል መርህን መከተሉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የለውጡ መንግስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመንግስት የስራ ኃላፊነቶች ላይ ማካተቱና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶችም ሊጠናከሩ የሚገባቸው ተግባራት መሆናቸውን አመልክተዋል።
ለሀገር የሚበጁ የተለያዩ ሀሳቦችን ወደ አንድ ማምጣት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት በመሆናቸው አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር መሀመድ አርባኢ በበኩላቸው፥ በለውጡ ዓመታት የታዩ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ተግባራት በሀገር ጉዳይ ተቀራርቦ መስራት እንዲለመድ መሰረት መጣላቸውን ተናግረዋል።
በትብብርና በጋራ የመሥራት እሳቤው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመገፋፋት ይልቅ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ትልቅ እገዛ አድርጓል ነው ያሉት።
ይህን የዴሞክራሲያዊ ልምምድን በማስቀጠል አሳታፊ የመንግስት ስርዓትን ማስቀጠል ለሀገራዊ እድገት የማይተካ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህን መልካም ጅማሮ በማስቀጠል 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስቀደመ አቋም ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።