ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፣  መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በለውጡ ዓመታት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት አንዱ በትምህርት ዘርፉ ያጋጠሙ ስብራቶችን ከመሰረቱ በመለወጥ ዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ማስቻል ነው።

ትምህርት ቤቶችን ማሻሻልና አዳዲስ ትምህርት በቶችን መገንባት፣ የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል፣ የትምህርት ግብዓት ማሟላት፣ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር እና  ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ማስፋት ደግሞ በዘርፉ ከተከናወኑ ተግባራት ዋነኞቹ ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ ካሳሁን ገላና(ዶ/ር) በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከሩን ገልጸዋል።

በክልሉ በዚህ አመት የትምህርት ገበታ ላይ ያሉ 180 ሺህ ተማሪዎች ፈተናውን የሚወስዱ ሲሆን  የተሻለ ነጥብ እንዲያስመዘግቡ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።

በዚህ መሰረት ከባለፉት አመታት ልምድ በመውሰድ በማጠናከሪያ ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የትምህርት አይነቶችን በመለየት ድጋፍ እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የመማር ማስተማር ሂደቱን ማጠናከር፣ ዋቢ መጽሃፍትን ማሟላት፣ ቤተ መጻህፍትና ቤተ ሙከራዎችን ማስፋትና ግብዓቶችን ማሟላት እንዲሁም ለመምህራን ስልጠና መስጠት በሰፊው ከተሰሩት መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ አሁን ላይ የመማር ማስተማር ተግባሩ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አንስተው፣ በቀሩት ወራት ደግሞ በመምህራን እገዛ ተማሪዎች በግልም ሆነ በቡድን የተለያዩ ጥያቄዎችን  የሚለማመዱበት ወቅት መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ በፊት ተማሪዎች መደበኛውን ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ እንደነበረ ያስታወሱት ምክትል ሀላፊው ዘንድሮ የተማሪዎችን ውጤት በተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ከመስከረም ወር ጀምሮ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም ለአዳሪና ልዩ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የበለጠ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በተለያየ ሁኔታ የማጠናከሪያና ሌሎች ድጋፎች መደረጉን ጠቅሰዋል። 

አጠቃላይ በክልሉ በ1ሺህ 406 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በተሻለ ሁኔታ እያዘጋጀን ነው ብለዋል።

በተለይ ለሴት ተማሪዎች በጋራ ከሚደረግላቸው ድጋፍ በተጨማሪ እራሳቸው በመረጡት የትምህርት አይነት ላይ በተመረጡ መምህራን የተለየ የማጠናከሪያ ድጋፍ እያገኙ መሆኑን አንስተዋል።

የተማሪዎችን ውጤት ከማሻሻል ረገድ የወላጆች እገዛ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፣ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ከወላጅ ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም