የመንግስት ያላሰለሰ የሰላም ጥረትና የታጣቂዎች በጎ ምላሽ ዘላቂ ሰላም እያመጣ ነው-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ያላሰለሰ የሰላም ጥረትና የታጣቂዎች በጎ ምላሽ ዘላቂ ሰላም እያመጣ ነው-ነዋሪዎች
ወልድያ፤መጋቢት 23/2018 (ኢዜአ)፦የመንግስት ያላሰለሰ የሰላም ጥረትና የታጣቂዎች በጎ ምላሽ ዘላቂ ሰላም እያመጣ መሆኑን በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በጫካ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ከግጭት ወጥተው የሰላምን አማራጭ ተቀብለው እንዲመጡ መንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ አመራሮችና አባሎቻቸው ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላም መጥተዋል።
ከዚህ በፊት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ፣ኮሎኔል ፋንታሁን ሙሃባ እና ሌሎችም የሰላምን መንገድ መርጠው መምጣታቸው ይታወሳል።
በትናንትናው እለት ደግሞ በክልሉ የሚንቀሳቀሰውና ራሱን አፋብን ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ሃይል ወታደራዊ አዛዥ ኮማንዶ ፍቅሩ ሙሉዬ ከመንግስት የተደረገለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ከእነ አጃቢዎቹ ላሊበላና አካባቢው ወደ ሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት በሰላም መግባቱ ይታወቃል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ በላይ ገረመው እና አቶ ሲሳይ ጸጋዬ፤ በተለይም የመንግስት ያላሰለሰ የሰላም ጥረት ትልቅ ስኬት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ታጣቂዎችና አመራሮቻቸው ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸው በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተደረገ ያለውን ጥረት እውን የሚያደርግ ይሆናልም ብለዋል።
በዞኑ ላሊበላ ከተማ የሚኖሩት አቶ ሲሳይ ታደሠ፤በላስታና አካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረውን ፅንፈኛ ቡድን የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ መምጣቱ ለአካባቢው ነዋሪ ትልቅ እፎይታ መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢው ቀደም ሲል የነበረው ግጭት በነዋሪው ዘንድ ብዙ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰው፥ በመንግስት ተደጋጋሚ ጥረት፣በህዝቡ የሰላም ጽኑ አቋም የሚፈለገው ውጤት በመምጣቱ ተደስተናል ብለዋል።
ከግጭት ጥፋትና ውድመት እንጂ አንዳችም የሚመጣ ለውጥና የሚገኝ ውጤት እንደሌለ ባለፉት አመታት አይተነዋል ያሉት አቶ ሲሳይ ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም አለብን በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዞኑ በመቄት ወረዳ የ029 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ በላይ ተሻለ እና በግዳን ወረዳ የሚኖሩት አቶ ዘውዱ አስራደ፤ የእርስ በርስ ግጭት ትርፉ ልማትን ማውደም፣ የወንድማማችነት ትስስርን ማበላሸትና ማህበረሰብን መጉዳት እንጂ ሌላ ትርፍ የሌለው መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የታጣቂ ቡድኖች በመንግስት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ጊዜ ሳያጠፉ ተቀብለው በመምጣት ማህበረሰቡን በመቀላቀል በሰላም መኖርን መምረጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ በላስታና አካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረውን ፅንፈኛ ቡድን ወታደራዊ አዛዥ የነበረው ኮማንዶ ፍቅሩ፤በትናንትናው እለት የመንግስትን ጥሪ ተቀብሎ መምጣቱ ለአካባቢው ነዋሪ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በጫካ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ ሽፍቶች የመንግስትን የሰላም አማራጭ መቀበላቸው ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልጸው፥ ሌሎችም ወደ ሰላም እንዲመጡ ጠይቀዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ መብራቱ አሰፋ፤ በዞኑ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በተለይም በቡግና፣ላሊበላ፣ ላስታ፣ መቄትና ግዳን ወረዳዎች ለሚገኘው ህዝብ የሰላም እፎይታ የሰጠ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የመንግስት ያላሰለሰ የሰላም ጥረት እንዳለ ሆኖ የአካባቢው ህዝብ ለሰላም ያሳየው ጽኑ አቋምና የሰላም ጥረት ለስኬቱ ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይም መሰል ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።